ቀጥታ፡

ጉባኤው የጋራ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማጉላት የሕዝቡን አብሮነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለጸ

ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጋራ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማጉላት የሕዝቡን አብሮነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለጸ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተመስርቷል።

የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ ተደርገው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ መልከ ፄዴቅ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዝሀ ሀይማኖት፣ ብሄርና ባህል ባለቤት ናት ብለዋል።


 

አዲስ የተመሰረተው የክልሉ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮችን በማበልፀግ የዜጎችን አብሮነት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

''ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት የሆነ የፈጣሪ ስጦታ ነው'' ያሉት ብፁዕ አቡነ መልከ ፄዴቅ ለሰላም መጠበቅና መጠናከር የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ሀይማኖታዊ አስተምሮን ተግባራዊ ማድረግ ሰላምን በተቀናጀ መንገድ ለማስጠበቅ የጉባኤው መመስረት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ሀጂ መሀመድ ኸሊል ናቸው።

አንድነትና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ጠቃሚ ስራዎችን በመስራት ለሀገር ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት እንደሚተጉም ተናግረዋል።

በክልሉ አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዙ ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው የሰው ልጆችን ማህበራዊ ግንኙነት በማጎልበት ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሀይማኖት ተቋማት በሰላም፣ በአብሮነት፣ በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረቱ መልካም እሴቶችን በማጠናከር የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲሳካ ማገዝ አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም የሀይማኖት ተቋማት በስነ-ምግባርና ግብረ ገብነት የተላበሱ ዜጎችን ማፍራት ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው ሊንቀሳቀሰሱ  እንደሚገባም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም