የባቡር ትራንስፖርቱ እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግድ ምርት በማጓጓዝ የአገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባቡር ትራንስፖርቱ እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግድ ምርት በማጓጓዝ የአገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ) ፦ እያደገ የመጣውን አገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ ምርት በማጓጓዝ የአገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ የባቡር ትራንስፖርቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ተናገሩ።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መነሻ የሆነው የሰበታ ባቡር ጣቢያ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ እንዳሉት፤ የባቡር ትራንስፖርቱ እያደገ የመጣውን የወጪ ምርት ወደ ውጪ በማጓጓዝ እና መሰረታዊ ገቢ ምርቶችን በፍጥነት እንዲደርሱ እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ ምርቱ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የአገሪቱን ወጪ እና ገቢ ምርቶች በባቡር ትራንስፖርት እየተጓጓዝ ያለው 15 በመቶ አካባቢ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር ሰበታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የባቡር ጣቢያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃው ተናግረዋል።
የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ፤ በኢትዮጵያና ጂቡቲ የተለያዩ ከተሞች 20 ባቡር ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን አዳዲስ ጣቢያዎችን በመክፈት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰበታ የባቡር ጣቢያው ስራ መጀመር ለሸገር ከተማ ነዋሪዎች ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ ጉግሳ ደጀኔ በበኩላቸው የሰበታ ባቡር ጣቢያ ስራ መጀመር ለአካባቢው ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተናግረዋል።
የባቡር ትራንስፖርቱ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀም በመሆኑ ለከተማዋ የስማርት ትራንስፖርት ትግበራ ጥሩ ማሳያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት በኢትዮጵያ እና ጂቡቲ መንግስታት እ.ኤ.አ 2018 የተመሠረተ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለውን ጭነት እና ሰዎችን በማጓጓዝ ለሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።