የከተራና ጥምቀት በዓል የመቻቻልና የአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የከተራና ጥምቀት በዓል የመቻቻልና የአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አካሂደዋል።

በአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ  ምክትል ኃላፊ ፍቅሬ ግዛው በምክክሩ ላይ እንዳሉት፤ የከተራና ጥምቀት በዓላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ ነው።


 

የዘንድሮው የከተራና ጥምቀት በዓል በመቻቻልና በአብሮነት እሴትን ጠብቀው እንዲከበሩ ቢሮው አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።

ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላትና የከተማዋ ነዋሪዎች  ጋር በመቀናጀት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን  የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የሃይማኖት አባቶች፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ከወዲሁ  ትኩረት በመስጠት መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የከተራና ጥምቀት በዓላት በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከኢትዮጵያውያን አልፎ የውጭ አገር ዜጎች በመታደም የሚያከብሩት  ነው።


 

በዓላቱ የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ ትስስር፣ ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

የ2016 ዓ.ም. የከተራና ጥምቀት በዓላት በከተማችን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲከበር የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ  የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ አባቶች የዘንድሮው  የከተራና ጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ አባቶቹ  አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በዓሉ በሰላም እንዲከበር እያደረጉት ላለው ቅድመ ዝግጅት ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም