ቀጥታ፡

መከላከያ ሠራዊትን ማገልገል ኢትዮጵያን ማገልገል ነው - የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ) ፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማገልገል ኢትዮጵያን የማገልገል ድርብ የክብር ኃላፊነት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ተናገሩ።

በመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ የጦር ኃይሎች አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተቋሙን ለረዥም ዓመታት ላገለገሉ እና የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ ሙያተኞች እውቅና ሰጥቷል።


 

በእውቅና መርሃ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የመከላከያ ሠራዊት የሰው ኃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀጫሉ ሸለመ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የሕክምና ሙያተኞች ተገኝተዋል። 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ ኢትዮጵያን በቅንነት ላገለገሉና እያገለገሉ ለሚገኙ የሆስፒታሉ ሙያተኞች እውቅና መስጠት የሚያኮራ ተግባር ነው ብለዋል።

ሙያተኞቹ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን አገር መከላከያ ሠራዊትን  በታታሪነትና በሀገር ፍቅር በማገልገላቸው ልዩ ክብር የሚሰጠው እውቅና መሆኑንም ገልጸዋል።

ዕውቅናው የህክምና ሙያተኞችን በቀጣይ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማነሳሳት የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

መከላከያ ሠራዊትን ማገልግል ኢትዮጵያን የማገልገል ድርብ የክብር ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሙያተኞቹ ለሠራዊቱ ላበረከቱት ሙያዊ እገዛ አመስግነዋል።

የጦር ኃይሎች አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዶክተር ኃይሉ እንደሻው፤ ሆስፒታሉ ልዩ ልዩ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ የ80 ዓመት አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል። 

በየዘመኑ በእውቀት፣ በቅንነትና ታማኝነት ወገናቸውን ላገለገሉ አንጋፋ ሙያተኞችና አሁንም በስራ ላይ ሆነው የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ  ሰራተኞች እውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ይበልጥ ለማጠናከር ለማዕከላት ማስፋፊያ፣ ስፔሻሊስት ሙያተኞችን ለማፍራትና ለቴክኖሎጂ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።


 

ከተሸላሚዎች መካከል ተቋሙን ለ40 ዓመታት ያገለገሉት ኮሎኔል ዶክተር ንጉሴ ተፈራ፤ ሆስፒታሉ በጡረታ የተሸኙ ሙያተኞች ሀገራቸውንና ሠራዊቱን ላገለገሉበት የተሰጠ ክብር ነው ብለዋል።

በሆስፒታሉ የነርቭ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ናርዶስ አሰፋ፤ እውቅናው ሙያዊ ኃላፊነትን በበለጠ ትጋት ለመወጣት የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአንጎልና ኅብረሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሸምሰዲን ሙሰፋ፤ በጡረታ ለተሰናበቱ እና በስራ ላይ ላሉ ሙያተኞች በአንድ መድረክ እውቅና መሰጠቱ ሠራዊቱን የበለጠ ለማገልገል ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከአንገት በላይ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶክተር ጽጌሬዳ አትሞ እንዳሉት፤ በአርዓያነት ከሚጠቀሱ የቀድሞ ሙያተኞች ጋር መሸለማቸው ሠራዊቱን በበለጠ ትጋት ለማገልገል ብርታት እንደሚሰጣቸው  ተናግረዋል። 

በሰሜኑ ጦርነት የህልውና እና የሰላም ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ላስተናገዱ የሠራዊት አባላት ሲሰጥ በነበረው የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ ሲያደርጉ ለነበሩ የሕክምና ተቋማትም ምስጋና ቀርቧል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም