ቀጥታ፡

በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው የምርጥ ዘር ምርት እየተሰበሰበ ነው 

ሚዛን አማን ፤ ታኅሣሥ 11/2016 (ኢዜአ) :-በሀገሪቱ ለ2016/17 የምርት ዘመን የሚሆን በ20ሺ ሄክታር መሬት ላይ የለማ የምርጥ ዘር ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ሀገራዊ የዘር ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ የሚያመርተውን የምርጥ ዘር ምርት መጠን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።


በኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘርና ደን ውጤቶች ልማት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ እየጨመረ የመጣውን  የምርጥ ዘር  ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው።

በዚህም በ22 ሰብሎች ላይ የምርጥ ዘር ብዜትና አቅርቦት ሥራ በማከናወን 96 ምርጥ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።


በተያዘው የምርት ዘመንም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘርን በማልማት 473 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ 40 በመቶ የሚሆነው ምርጥ ዘር መሰብሰቡንና ቀሪውም በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኮርፖሬሽኑ ባለፈው  የምርት ዘመን ከ388 ሺህ  ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር አምርቶ በ25 የምርጥ ዘር አቅርቦት ማዕከላት በኩል ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን አቶ ዘነበ  አስታውቀዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ የዘር ብዜት እርሻን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን  ያስረዱት ሥራ አስፈጻሚው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሁለተኛ የምርጥ ዘር ብዜት የእርሻ ጣቢያውን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን በሚገኘው ታማሻሎ የምርጥ ዘር ብዜት እርሻ ጣቢያ ላይ የሩዝ፣ የማሽላ የስንዴና የቦሎቄ ዘር ተባዝቶ ከፊሉ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በኮርፖሬሽኑ የቦንጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስረስ አስፋው ከጣቢያው አምና  ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን  አስታውሰዋል።


 

በተያዘው የምርት ዘመን ደግሞ ከጣቢያው ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይጠበቃል ብለዋል።

እስካሁን ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪው በአንድ ወር ውስጥ ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

በጣቢያው ከሚባዛው በተጨማሪ በኮንትራት እርሻ ከተባዛው ከ6 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚሰበሰብ አቶ አስረስ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ተደራሽነቱን በማስፋቱ ዘር በማጓጓዝ የሚወጣ ገንዘብና ጊዜን ማትረፍ አስችሏል ብለዋል።

የታማሻሎ ምርጥ ዘር ብዜት ጣቢያ ወደ ምርት መግባቱ በክልሉ  የተሻለ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር እንዳገዘ አመላክተዋል።

 በጣቢያው የሚካሄደው የዘር ብዜት እየተስፋፋ ሲሄድ ከክልሉ አልፎ ለሌሎች አካባቢዎች የሚተርፍ  ምርጥ ዘር ይመረታል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

 


 

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም