በዞኖቹ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ

ደብረ ብርሃን/ ደሴ ፤ ታህሳሥ 11/2016 (ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞኖች በበጋ ወራት በ83 ሺህ 280 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን የየዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።

በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተያዘው የበጋ ወራት የአርሶ አደሩን ጉልበት በመጠቀም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።

በዚህም ከዚህ በፊት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ባልተሸፈነ በ23 ሺህ 280 ሄክታር መሬት  ላይ ዘንድሮ ለመስራት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።

በልማት ስራውም የማሳ እና የተራራ ላይ እርከን፣ የቦረቦር ልማት ስራ እና ሌሎች ልዩ ልዩ የርጥበት እቀባ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የስራ መሳሪያ የመለየት፣ የሰው ሃይል የማደራጀት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በልማት ስራውም  459 ሺህ 730 ሰው እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል።

በበጋ ወራት የሚከናወነውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በቀጣዩ የክረምት ወቅት በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር 283 ሚሊዮን ችግኝ የማዘጋጀት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

ከአሳግርት ወረዳ የታሞ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ተራራማ አካባቢዎችን እርከን በመስራትና ችግኝ በመትከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያገኙ እንደሆነ ገልፀዋል። 

በተሰሩ ስራዎች የጎለበቱ ምንጮችን በመጠቀም ሸንኮራ አገዳ፣ ጌሾ፣ ቀይ ሽንኩርትና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን በማልማት በዓመት እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ ገቢ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። 

በዚህ የበጋ ወራትም የአካባቢያቸውን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው አርሶ አደር ዘነበ ገብረመድህን በበኩላቸው፤ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀደሙት ዓመታት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራዎች የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግራቸውን ከመፍታቱም ባለፈ የደን ሃብቱ መልሶ እንዲተካ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህ የበጋ ወቅትም ልማቱን በተደራጀ አግባብ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።  

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን በበጋው ወራት በ60 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ናቸው።

የልማት ስራው የሚከናወነው በ1 ሺህ 400 በተመረጡ ተፋሰሶች ውስጥ ሲሆን፤ ለስራው አስፈላጊ የልማት መሳሪያዎች ተለይተው ለቀያሽ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ልማቱ ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ለተከታታይ 30 ቀናት የሚከናወን ሲሆን፤ ከ600 ሺህ ህዝብ በላይ እንዲሳተፍ በየደረጃው ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል "የዚህ ዓመት የበጋ ወራት የልማት ስራም በተደራጀ አግባብ ይከናወናል" ብለዋል።

በመጪው ክረምትም በ33 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል 260 ሚሊዮን ችግኝ እየተዘጋጀ እንደሆነም አመልክተዋል።

በአማራ ክልል በዚህ የበጋ ወቅት ህብረተሰቡን በማስተባበር ጠንካራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም