"የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" ዓመታዊ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" ዓመታዊ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2016(ኢዜአ)፦በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት የቆየውና የዳኝነት ሥርዓት ለማጠናከር የተቋቋመው " የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ " ዓመታዊ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ነባር ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ሲሆን፤ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቤተ-ጉራጌ ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲገለገልበት የቆየ ነው።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ይህ ቅርስ ግጭት ለማርገብ፣ ቂም በቀልን ለማሻር፣ የሰው ሕይወትና ኃብት ንብረት ከአደጋ ለመጠበቅ፣ ሰላማዊ፣ ጤናማ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠርና ፍትሕን ለማስፈን ይጠቀሙበታል።
ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ባለው ጠንካራ ባህላዊና ትውፊታዊ መሠረት አኳያም በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የታፈረ ሥርዓት ነው።
የቤተ-ጉራጌ የዳኝነት ሥርዓት የተግባር አንድነት ቢኖረውም እንደየአካባቢው ልዩ ልዩ የስያሜ አጠራሮች አሉት።
ለአብነትም በሰባት ቤት ጉራጌ "የኧጆካ ቕጫ"፣ በክስታኔ እና በወለኔ ቤተ-ጉራጌ "የጎርደና ሴራ"፣ በመስቃን ቤተ-ጉራጌ "የፈር አገዘኘ ሴራ" እንዲሁም በዶቢ ቤተ-ጉራጌ "የዶቢ ጎጎት ስናኖ ሴራ" በመባል ይታወቃሉ።
ከአራት ዓመታት በፊት ሁሉንም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች የሀገር ሽማግሌዎችን በማሰባሰብ 'የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ" ተቋቁሟል።
በዚህም የዘንድሮው ባህላዊ ሸንጎ ጉባዔም የጉራጌ እና የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የራሱ መተዳደሪያ ደንብ ያለው የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ 60 ጠቅላላ ጉባዔ አባላት እና ለሦስት ዓመታት በምርጫ የሚያገለግሉ የ15 ሥራ አስፈጻሚ አባላት አሉት።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ፤ የጉራጌ ባህል ሸንጎ የጉራጌ ሕዝብን የሚያስተሳስር ትልቅ እሴት መሆኑን ጠቁመዋል።
የሽምግልና ሥርዓቱ የጉራጌን የከበረ ባህል ያሳየና ለዘመናት የቆየ የሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅ ያደረገ እሴት መሆኑን ገልፀዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው፤ አባቶች እና ጉባዔተኞች የጉራጌ ሕዝብ አንድነትና አብሮነት እንዲጎለብት በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የጉራጌ ባህልና እሴቶች፣ ታሪክና ቅርሶችን በማዳበርና ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት በመሥራት የቱሪስት መስህብ እንዲሆንና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲያድግ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።