ቀጥታ፡

ባህርዳር እና የቻይናዋ ዱጃንየ ከተሞች የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ታህሣሥ 11/2016 (ኢዜአ)፡- ባህርዳር እና የቻይናዋ ዱጃንየ ከተሞች የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው ልዑክ በቻይና ቼንዱ ከተማ እያደረገ ባለው የስራ ጉብኝት የባህርዳር እና ዱጃንየ ከተሞች ዛሬ የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው እና የዱጃንየ ከተማ ከንቲባ ጃንያ ዳን ስምምነቱን መፈረማቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በዚህም በቀጣይ ሁለቱ ከተሞች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በፓርክ ልማትና አስተዳደር እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ዙሪያ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል።


 

በተጨማሪም በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ የቻይና የፓርክ ከተማ ተብላ በምትታወቀው ቼንዱ ከተማ የተለያዩ ፓርኮችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳለማው፣ የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች መሳተፋቸውም በመረጃው ተመላክቷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር ለመስራት የቻይና ከተሞች ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም