የሀይማኖት ተቋማት የሰላምና የአብሮነት እሴት ግንባታን በማጎልበት በኩል ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

ሆሳዕና ፤ ታህሣሥ 11/2016 (ኢዜአ)፡- የሀይማኖት ተቋማት የሰላምና የአብሮነት እሴት ግንባታን በማጎልበት በኩል ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የምስረታ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት፤ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት በማጎልበት የበለጸገች አገር ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሀይማኖት ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በተለይም ሰላምንና አብሮነትን በማጽናት በኩል የሚኖራቸው ተግባር ከመደበኛ ተግባራቸው ተለይቶ የማይታይ መሆኑን አመልክተው፤ ተቋማቱ ያለባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የተለያዩ ሀይማኖቶችና እምነቶች ተከባብረው ሰላማቸውን ጠብቀው የሚኖሩበት እንደሆነም አብራርተዋል።

የእያንዳንዱ ሀይማኖት አስተምህሮ ተከብሮና ተጠብቆ በጋራ በአብሮነትና በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል።

የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታም አንዱ ዓላማ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

ሁሉም ሀይማኖቶች በሰዎች መካከል ሁሌም ሰላማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነት እንዲዳብር በአፅንኦት እንደሚያስተምሩም ጠይቀዋል።

የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች ይህንን አስተምህሮ መሰረት በማድረግ ስለ ሰላም ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የገለፁት።


 

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፤ የአካባቢውን ህዝብ አብሮነት በማጠናከር የሰላም ተምሳሌት የሆነ ክልል ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

የእምነት ተቋማት የህዝቦችን ተቻችሎ የመኖር እሳቤን ሰላምና አብሮነት አስጠብቆ በማስቀጠል የሚጠበቅባቸው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ይህን ተግባራቸውን በማስቀጠል ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት እያደረጉት ያለውን ጥረት እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የምስረታ ጉባኤ ላይ ከክልሉ የተውጣጡ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም