የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የሰበታ ባቡር ጣቢያን ስራ አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የሰበታ ባቡር ጣቢያን ስራ አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መነሻ የሆነው የሰበታ ባቡር ጣቢያ ተመርቆ ስራ ጀመረ።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፣ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ፣ የሸገር ከተማ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ ዴንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን ወጪና ገቢ ንግድ ምርት ለማጓጓዝ የባቡር ትራንስፖርቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።
በተለይ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር ሰበታ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የባቡር ጣቢያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃው ተናግረዋል።
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ፤ በኢትዮጵያና ጅቡቲ የተለያዩ ከተሞች 20 ባቡር ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን አዳዲስ ጣቢያዎችን በመክፈት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰበታ የባቡር ጣቢያው ስራ መጀመር የአዲሱን የሸገር ከተማ ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መንግስታት የተመሠረተ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለውን ጭነት እና ሰዎችን በማጓጓዝ ለሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡