የዓይን ብርሃንን ዳግም የማግኛ ዕድል - ኢዜአ አማርኛ
የዓይን ብርሃንን ዳግም የማግኛ ዕድል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2016(ኢዜአ)፦ በዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ማየት የተሳነውን የዓይን ብርሃን ዳግም የማግኛ ዕድል
ወጣት ሜላት ተሰማ ትውልድና እድገቷ አዲስ አበባ እንደሆነ ትናገራለች።
እድሜዋ ለሥራ ሲደርስ የመስተንግዶ ሥራ በሆቴል እየሰራች፤ ጎን ለጎን የአካውንቲንግ ትምህርት በመማር ሕይወቷን ለመምራት ጥረት ማድረግ ጀመረች።
ይሁንና ከአምስት ዓመት በፊት በደረሰባት የአሲድ ጥቃት በቀኝ ዓይኗ ላይ የዓይን ብሌን ጠባሳ አጋጠማት።
በተለይም በዓይኗ ላይ በተፈጠረው ችግርም ያሳደረባት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጫና ቀላል እንዳልነበረ ታስታውሳለች።
ሜላት በወቅቱ የገጠማትን ሁኔታ መቀበል ከብዷት እንደነበር ገልፃ፤ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ከተደረገላት ማየት እንደምትችል ከሕክምና ባለሙያ ሲነገራት ተስፋዋ እንደለመለመ ገልጻለች።
የሕክምና ክትትል ስታደርግ ከነበረበት በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የነበራት ጉጉት ከፍተኛ እንደነበር ተናግራለች።
ወጣቷ በጎ ፈቃደኞች ከመሞታቸው በፊት የዓይን የብሌን ልገሳ ለማድረግ በሚገቡት ቃል መሠረት የዓይን ብርሃኗን ከአራት ዓመት በላይ የሕክምና ክትትል በኋላ ዳግም አግኝቻለሁ ስትል ገልጻለች።
ዜጎች ስለ ዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት እንዲቀየር ለማድረግ ግንዛቤ እንዲያገኙ እያደረገች መሆኑን ተናግራለች።
የሕክምና አገልግሎቱ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በርካታ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ የዓይን ብሌን የመለገስ ባህሉን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርባለች።
በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ባደረጉለት የዓይን ብሌን ልገሳ ብርሃኑን ዳግም ማግኘት የቻለው ወጣት ታሪኩ ሁሴን ይባላል።
ወጣት ታሪኩ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው።
የቀኝ የዓይን ክፍሉ ላይ ሕመም ያጋጠመው ከስድስት እስከ ሰባት ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ያስታውሳል።
በሕክምና አለርጂክ እንዳጋጠመውና ከጊዜ በኋላ ከሕመሙ እንደሚድን በባለሙያዎች ቢነገረውም መዳን እንዳልቻለ ያስታውሳል።
ሕመሙ ሲበረታበት በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ላይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምናውን ማድረግ እንደጀመረ ይናገራል።
ከበጎ ፈቃደኞች ባገኘው የዓይን ልገሳ በተደረገለት የዓይን ብሌን ንቀለ ተከላ ሕክምና ዳግም ብርሃንን የማየት ዕድል ማግኘቱን ጠቅሷል።
ማኅበረሰቡ እንደ ደም ልገሳ ሁሉ የዓይን ብሌን ልገሳን ባህሉ ሊያደርግ እንደሚገባም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ፤ ተቋሙ በ2015 ዓ.ም በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ለ108 ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ለማድረግ ታቅዶ 100ዎቹ ሕክምናውን እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል።
የተደረገው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የሚበረታታ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ከፊታችን ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ የሚያመለክት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ሕብረተሰቡ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ለጋሾች በኢትዮጵያ ባሉ ደም ባንክ ቅርንጫፎች ቃል መግባት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በተመረጡ የክልል ከተሞች ዓይን ለመለገስ ቃል የገቡ ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ተገልጋዮች ወዲያው የሚጠቀሙበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ 20 ዓመት ባስቆጠረው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት እስካሁን ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።