የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁሉንም ዓይነት ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን - የጂንካና የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁሉንም ዓይነት ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን - የጂንካና የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች

ጂንካ/አርባ ምንጭ፤ ታኀሳስ 11/ 2016 (ኢዜአ)፡ - የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁሉንም አይነት ጥረቶችን በማድረግ ከበሽታው ተጋላጭነት ራሳችንን እየጠበቅን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጂንካና የአርባምንጭ ከተሞች ነዋሪዎች ተናገሩ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ህብረተሰብን ያሳተፉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
የሁለቱም ከተሞች ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመግታት የአልጋ አጎበር ከመጠቀም እስከ አካባቢ ፅዳት ያሉትን ተግባራት በትጋት እያከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪው ጡረተኛ ዋና ሳጅን ዘውገ ኃይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወባ በሽታ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ለወባ ትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ ሰፍራዎችን በጋራ እያፀዱ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተሰጣቸውን የአልጋ አጎበር ሁልጊዜ በአግባቡ እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የጂንካ ከተማ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ስንቄ ታመነ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የወባ ትንኝ ንድፊያ መከላከያ የሆነውን የአልጋ አጎበር ባለመጠቀማቸው ለወባ በሽታ በተደጋጋሚ ሲጋለጡ እንደነበር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በጤና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክር የአልጋ አጎበር መጠቀም መጀመራቸውን ገልፀው ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ እንዳይሆንም አካባቢያቸውን እያፀዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከወባ በሽታ መጠበቅ መቻላቸውንም ገልፀዋል።
አሁን ላይ እየታየ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት በመከላከል የራሳችንን ጤንነት ለመጠበቅ ሁሉንም ዓይነት ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሣራ ተፈራ ናቸው።
በተለይም ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የማጽዳት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተሰጣቸው ግንዛቤ መሰረትም የአልጋ አጎበርን በጥንቃቄ እየተጠቀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሌላኛዋ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች አሽኔ በበኩላቸው በጤና ባለሙያዎች ምክር በመታገዝ አጎበርና ኬሚካልን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን ራሳቸውን ከወባ በሽታ እየተከላከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አክለውም አንዳንድ ነዋሪዎች ይህንን ችላ በማለት ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆናቸው የቁጥጥርና የግንዛቤ ሥራዉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቋሚ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የወባ ትንኝ የማጥፋት ዘመቻው በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እየተካሄደ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ጤና ማበልፀግ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዳዊት ኩስያ ናቸው።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በመጨመር፣ ለትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ማፅዳት፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስና ማድረቅ፣ የግንዛቤ ሥራዎችን ማሳደግ በዘመቻ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።
በዚህም በክልሉ ለወባ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ 117 ቀበሌዎችን በመለየት ከ85 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ላይ የወባ ትንኝ ማጥፊያ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ የወባ ትንኝ ዕጭ በሚገኝባቸው ስፍራዎች ''አኳቲን'' የተሰኘ ፀረ-ዕጭ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎች በሚካሄድባቸው እንደ ደቡብ ኦሞ ያሉ ቆላማ አካባቢዎች ለወባ በሽታ መራባት አመቺ በመሆናቸው የበሽታውን ስርጭት ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተፈጻሚ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከአምና ጀምሮ ህብረተሰቡን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ በተሰሩ መጠነ ሰፊ ስራዎች ከ3 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበሮች ስርጭት መካሄዱን አስታውሰው፤ በዚህም ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ከበሽታው መጠበቅ መቻሉን ገልፀዋል።
የአካባቢ ንጽህና ጥበቃና የመድኃኒት ስርጭት በማከናወን በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው ነዋሪው በየአካባቢው እያደረገ ያለውን ጥረት ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል የአንድ ወር ህዝባዊ የንቅናቄ ሥራ ከታህሳስ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።