ቀጥታ፡

የጅቡቲ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ንግግር ያደርጋሉ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 11/2016 (ኢዜአ)፦ የጅቡቲ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በዛሬው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ተገለፀ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ ይካሄዳል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በጉባዔው ላይ የጅቡቲ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ድልኤታ መሀመድ ድልኤታ ንግግር ያደርጋሉ።

የኢፊዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከትላንት በስቲያ በቦሌ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለልዑካን ቡድኑ አባላት አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ ትላንት ረፋድ ላይም በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ተገኝተው ከአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ከኢትዮ-ጅቡቲ የወዳጅነት ቡድን ጋር ከተወያዩ በኋላ፤ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም