ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ጂቡቲ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማጠናከር የሁለቱ አገራት ፓርላማዎች በጋራ ይሰራሉ  

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ጂቡቲ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማጠናከርና በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሁለቱ አገራት ፓርላማዎች በጋራ እንደሚሰሩ ተገለጸ።  

በጂቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሃመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ  ታገሰ ጫፎ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል።

ውይይቱም ሁለቱ አገራት ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ማጠናከር በሚችሉባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ ተጠቅሷል።  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገራት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው። 

አገራቱ በምጣኔ ኃብትና በማኅበራዊ ዘርፎች የዳበረ አጋርነት እንዳላቸው ጠቅሰው ይህን ግንኙነት በሁሉም መስኮች ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ዛሬ ከጂቡቲ አቻቸው ጋር በጉምሩክና በተያያዥ ጉዳዮች የሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶችን ለመፍታት ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። 

በጂቡቲ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን  ጉዳይ ና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በተመለከተም ውጤታማ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።  

ውይይቱም የሁለቱ አገራት ስትራቴጂክ አጋርነትን የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።


 

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጥላ ሥር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከመግባባት መደረሱንም ተናግረዋል።

የጂቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሃመድ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሻ ገልጸዋል። 

አገራቱ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመሥራት የደረሷቸው ሥምምነቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ የየአገራቱ ፓርላማ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

ከዚህ አንጻር የአገራቱን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

በጂቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሃመድ የተመራው ልዑክ ቡድን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎብኝቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም