ዩኒቨርሲቲው የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል የሚችል የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ግልጋሎቶች ለማዋል የያዘችውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል የሰው ኃይል ልማት ላይ በማተኮር እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለተለያዩ የልማት ስራዎች ለመጠቀም የሚያስችላትን የፕሮቶኮል ስምምነት ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ተፈራርማ ወደ ስራ መግባቷ ይታወቃል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ልህቀት ማዕከላት ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው አዳም ለኢዜአ እንደገለጹት የኒውክለር ቴክኖሎጂ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኃይል ማመንጫና ለምግብ ማከሚያነት ያገለግላል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አገሪቱ በኒውክለር ኃይል ልማት የያዘችውን እቅድ ለማሳካት በዘርፉ ምርምሮችን ለማካሄድ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ነው።
ተቋሙ ካሉት ስምንት የልህቀት ማዕከላት የኒውክለር ሪአክተር ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል አንዱ መሆኑን አንስተው ማዕከሉ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ኮርያዊ ፕሮፌሰር ዶንግሶንግ ሶን እየተመራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ትምህርቱን በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና ከውጭ አጋሮች ጋር ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በመስጠት ማዕከሉን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የመጀመሪያ በሆነው የኒውክለር ሳይንስና ምህንድስ ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ አምስት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስረድተዋል።
በቀጣይ የልህቀት ማዕከሉ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ቁጥርና የሚሰጣቸውን ፕሮግራሞች በማሳደግ በዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ጥራት ያለው ትምህርትን እና ምርምርን ለማካሄድ በሩሲያና ኮሪያ ከሚገኙ የትምህርት እና ምርምር ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለልህቀት ማዕከሉ የሚመጥኑ የምርምር ግብአቶችን ለማሟላት የቅድመ አዋጭነት ጥናት እያካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የኒውክለር ሪአክተር ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል የህንጻ ግንባታ ተጠናቆ አስፈላጊ የምርምር እና የማስተማሪያ መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የሩስያ መንግስት በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኒውክለር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማትን በጋራ ለመስራት የሚያስችል የማዕቀፍ ስምምነት ማድረጋቸውም ይታወሳል።
በዚህም የኒውክለር ቴክኖለጂን በመጠቀም ለጤና፣ ለግብርናና መሰል ቴክኖሎጂዎች የሚውሉ ግብአቶችን ለማምረት የተስማሙ ሲሆን በተጨማሪ በሰው ሀይል ስልጠናና በኒውክለር የሀይል ማመንጫ ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይም ደርሰዋል።