ዳያስፖራው በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚኖረውን ንቁ ተሳትፎ የተመለከቱ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚኖረውን ንቁ ተሳትፎ የተመለከቱ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚኖረውን ንቁ ተሳትፎ የተመለከተ ተከታታይ ውይይት እያካሄደ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ኮሚሽኑ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተከታታይ የበይነ መረብ ውይይቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡
የውይይቶቹ ዋና ዓላማ የዳያስፖራ አባላት በሀገራቸው ጉዳይ ባለቤት በመሆናቸው ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓቶችን እንዲሰጡ ማስቻል ነው።
ኮሚሽኑ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር የዳያስፖራው አባላት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ንቁ ተሳትፎ እና ድጋፍ ውይይቶች አድርጓል።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያውያን ባልተግባቡባቸው መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸው ለሀገራችን መጻኢ ተስፋ አስፈላጊ እንደሆነ በመጠቆም ፣ ስለ ሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ፅንሰ-ሀሳብ፣ በኮሚሽኑ ስለተከናወኑ አንኳር ተግባራት እና ኮሚሽኑ ስለሚገዛባቸው የህግ ማዕቀፎች ላይ ገለጻ አቅርቦ ገንቢ ውይይቶች ተካሂደዋል።
የዳያስፖራ አባለቱም ለኮሚሽኑ የስራ እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገነው መረጃ ያሳያል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ መሰል ውይይቶችን በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተመሳሳይ ውይይቶችን እንደሚያካሂድ ተመልክቷል።