የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በህዝቦች መካከል አንድነትና መከባበር እንዲሰፍን አበክሮ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በህዝቦች መካከል አንድነትና መከባበር እንዲሰፍን አበክሮ ይሰራል
ሶዶ፤ ታህሳስ 10/2016 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በህዝቦች መካከል አንድነትና መከባበር እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አዲሱ የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ አስታወቁ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬው ዕለት በወላይታ ሶዶ ከተማ ተመስርቷል።
በጉባኤው ምስረታ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚያገለግሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስራ አስፈፃሚና ሌሎች የስራ ኃላፊዎችንም ተሹመዋል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ በህዝቦች መካከል አንድነትና መከባበር እንዲሰፍን የክልሉ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የሀገርን በጎ ገፅታ ለማጉላት ማህበራዊ ትስስራችንን ልናጠናክር ይገባል ያሉት ሰብሳቢው በዚህ ረገድም የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤው ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
በክልሉ ያለውን የሰላምና የአብሮነት ተሞክሮ ይበልጥ እንዲጠናከርና ልዩነቶች ላልተፈለገ ዓላማ እንዳይውሉ አባላቱ ከማስተማር ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ በተደራጀ መንገድ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
መድረኩን የታደሙት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በተፈጥሮ የተቸርናቸው ልዩነቶቻችንን እንደፀጋ መቀበል ይገባል።
"በመሆኑም የወንድማማችነት እሴትን ገንብተን ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት የምናስበውን ልማት ለማጠናከር ልንረባረብ ይገባል" ብለዋል።
በአቋራጭ መንገድ ሊበለፅጉ የሚፈልጉና የሀይማኖት ልዩነቶችን ለዓላማቸው ማሳኪያነት የሚጠቀሙ አካላት ፍላጎት እንዳይሳካ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሠላም ለሁሉም ወሳኝ መሆኑን አንስተው እንደ ሀገር እየተከናወኑ የሚገኙ የሠላም ግንባታ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ በየሃይማኖታችን አስተምህሮ ትውልዱን በሰላም አስፈላጊነት ላይ ማነፅ ይገባናል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የእርቅ፣ የሰላምና የሀይማኖት ዕሴቶችን በማጎልበት ለአብሮነት እሴት ግንባታ በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚጠበቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዲስ ለተመሠረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የ50 ሺህ ብርና የተለያዩ የቢሮ ቁሳቁሶችን በድጋፍ መልክ አበርክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተወካዮችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።