ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የአፍሪካን የተሳትፎ ኮታ ለማግኘት ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ነው- ፌዴሬሽኑ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሎምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የአፍሪካን የተሳትፎ ኮታ በሁለቱም ፆታዎች ለማግኘት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ዋና አሰልጣኝና የቡድኑ ተወዳዳሪዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የኦሊምፒክ ተሳትፎ እ.አ.አ በ2021 በጃፓን በተከናወነው የኦሊምፒክ ውድድር ይጀምራል። 

በወቅቱም ለጃፓን ኦሊምፒክ ማጣሪያ በሞሮኮ ራባት ከተማ በተደረገው የቴኳንዶ ወድድር ሠሎሞን ደምሴ በ58 ኪሎ ግራም ተወዳድሮ በማለፍ በጃፓን በተደረገው ኦሊምፒክ መሳተፉ የሚታወስ ነው።

ዘንድሮም በፓሪስ ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት በሴኔጋል ዳካር ከተማ ከየካቲት 2-3/2016 ዓ.ም የማጣሪያ ውድድር ይከናወናል።

ኢትዮጵያም በዚህ ማጣሪያ ውድድር ላይ የምትሳተፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ዋና አሰልጣኝ ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለማጣሪያ ውድድሩ ዝግጅት ቢጀመርም በቂ ጊዜ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ ክለብ ባለመቋቋሙ ውድድር ሲደርስ ተወዳዳሪዎችን ከየማሰልጠኛ ክለቡ በመምረጥ ወደ ዝግጅት የሚገባ መሆኑ ጊዜ እንደሚወስድም ጠቅሰዋል።

ፌዴሬሽኑ ባለው የተጣበበ  ጊዜ በማጣሪያ ውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ለኦሊምፒክ ማጣሪያ ተመርጠው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙት ፍፁም ዘውዴና መስከረም ዘመድኩን በተመሳሳይ የልምምድ ጊዜያቸው አጭር መሆኑን ተናግረዋል።

የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቀጣይ ብሔራዊ ክለብ ቢቋቋም፤ የውድድር መድረኮች ቢኖሩ እና ውድድር ሲመጣ በቂ የዝግጅት ጊዜ ቢኖር ስፖርቱን ውጤታማ  እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት።


 

ኢትዮጵያ በሴኔጋል ዳካር ከተማ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ የወርልድ ቴኳንዶ ማጣሪያ ውድድር በወንድ አራት፤ በሴት አራት፤ በድምሩ ስምንት ተወዳዳሪዎችን እንደምታሳትፍ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2024 በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር እስካሁን በአትሌቲክስና በውሃ ዋና እንደምትሳተፍ  አረጋግጣለች።

የውሃ ዋና ተሳትፎ ያገኘችውም ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሀገራት በሚፈቅደው የተሳትፎ ኮታ (ዩኒቨርሳሊቲ) አማካኝነት መሆኑን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም