ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሙከራ ትግበራ በቅርቡ ልትጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10 /2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሙከራ ትግበራ በቅርቡ እንደምትጀምር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በነጻ የንግድ ቀጣናው ለመሳተፍ ያወጣችው የምርቶች የዋጋ ተመንም በአፍሪካ የንግድ ሚኒስቴሮች ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱ ተገልጿል።

ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የአፍሪካ አገራት ወደ አገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥና ሌሎች ከቀረጥ ውጪ ያሉ ተግዳሮቶችን በሂደት በመቀነስ የአፍሪካ የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመ የንግድ ቀጠና ነው።  


 

ይህም አሁን ላይ ከ15 በመቶ በታች የሆነውን የአፍሪካ አገራት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2040 ከ15 እስከ 25 በመቶ እንደሚያሳድገው የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መረጃ ያሳያል። 

አሁን በሙከራ ደረጃ ያለው ይኸው የንግድ ቀጣና የአፍሪካ አገራት የአርስ በእርስ የገበያ እድል መስፋት የአፍሪካ የግብርና የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማነቃቃት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር የአገራቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በማስቀጠል ትልቅ እምነት ተጥሎበታል።    

ኢትዮጵያም በዚህም አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በተለይም የኢትዮጵያ ምርቶች በአፍሪካ ገበያ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት የማረጋገጥ ሥራዎች ስታከናውን ቆይታለች።  

ከዚህ ጎን ለጎን መሰረተ-ልማቶችን የማሟላት እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የምትልካቸው የምርት አይነቶች የመለየት የዋጋ ተመን የማዘጋጀት ሥራ ሲሰራ መቆየቱንም ነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ለኢዜአ የተናገሩት። 

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ በጥናት ላይ ተመሥርታ ያዘጋጀቸው የምርቶች የዋጋ ተመን በአፍሪካ የንግድ ሚኒስቴሮች ምክር ቤት በቅርቡ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመዋል። 

በአንጻሩ፤ ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያን በሚገቡ ምርቶች የዋጋ ተመን በተመለከተ ከሥምምነት ለመድረስ ከአገራቱ ጋር ድርድር እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

አሁን ላይ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በአሥር አገራት በሙከራ ደረጃ ላይ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ከወራት በኋላ የሙከራ ትግበራ እንደምትጀምር ጠቁመዋል።

የሙከራ ትግበራው ከየትኞቹ አገራት ጋር ይሁን እንዲሁም በምን አይነት ምርቶች ይጀመር የሚሉትን ጉዳዮች በቀጣይ በሚካሄዱ የሁለትዮሽና ሌሎች ውይይቶች የሚወሰን መሆኑን ተናግረዋል።  

የንግድ ቀጣናው ወደ ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲገባ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጨምሮ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላት ገልጸዋል።  

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አሁን ላይ 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር የሆነውን ጠቅላላ አህጉራዊ ምርት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2050 ወደ 29 ትሪሊየን ዶላር ያደርሰዋል ተብሎ ተገምቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም