ግብጽ የያዘችው አቋም ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣና የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የሚገድብ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ የያዘችው አቋም ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣና የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የሚገድብ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10 /2016(ኢዜአ)፦ ግብጽ በድርድሩ ላይ የያዘችው አቋም ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ ና የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የሚገድብ መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል አራት ዙር ድርድሮች መካሄዳቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ከፍተኛ ጥረት ያደረገች ቢሆንም በግብጽ በኩል መፍትሄ የማይሆኑ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ላይ የተመረኮዙ አቋሞች በማንጸባረቋ አራተኛው ዙር ድርድር ያለስምምነት ተቋጭቷል።
ይህንን ተከትሎም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመግለጫቸው፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን ሀገራት ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ በጋራ መልማትን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር የምታደርገው ድርድር ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ግብጽ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በአግባቡ ያልተመለከተና የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን መሰረት ያደረገ ሀሳብ ማንጸባረቋን ተናግረዋል።
የግብጽ አቋም የኢትዮጵያን የወደፊት የመልማት ፍላጎት የሚገድብ፤ በህግ ማዕቀፎች ላይ የተፃፉ አንቀጾችን የሚፃረር ሀሳብ በመሆኑ ድርድሩ ያለ ስምምነት ተቋጭቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ የተለያዩ አስታራቂ ሀሳቦችን ማቅረቧን የጠቀሱት አምባሳደር ስለሺ፤ ግብጽ ግን ድርድሩን የማስቀጠል ፍላጎት እንደሌላት አሳውቃለች ብለዋል።
ግብጽ ከአራተኛው ዙር ድርድር በኋላ ዛቻ የሚመስል አቋም ማንጸባረቋን ጠቅሰው፣ በጋራ ከመልማትና በሰላም ከመኖር ውጭ የተሻለ አማራጭ የለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት መፍታት የሚችሉት በድርድር ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ የመልማት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ገልፃለች ያሉት አምባሳደር ስለሺ፤ አብሮ መልማትና ቀጣናዊ ትስስር እንፍጠር የሚለው የማይለወጥ አቋሟ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ግብጽ በኩል በድርድርና በስምምነት ሽፋን የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን ለማስፈፀም የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም ብለዋል።