የብዝሃ ኢኮኖሚ ስንቆቻችን (ኮይሻ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ ፣ ሃላለ ኬላ፣ ወንጪ ደንዲ፣ ጎርጎራ ...) - ኢዜአ አማርኛ
የብዝሃ ኢኮኖሚ ስንቆቻችን (ኮይሻ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ ፣ ሃላለ ኬላ፣ ወንጪ ደንዲ፣ ጎርጎራ ...)

የብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አይነተኛ ሚና አለው። በብዝሃ የኢኮኖሚ መስኮች በሚፈጠሩ አይነተ ብዙ እድሎች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሀብት መፍጠር ይቻላል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ በሰጠችው ልዩ ትኩረት እምርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች። በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመትም 6 ነጥብ 4 ከመቶ ጥቅል የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 ያስመዘገበችው እድገትም ከምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት፣ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ እንዳስቻላት የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል።
የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና የቱሪዝም መስኮችም ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎቿ ናቸው። በዚህ ላይ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ሲታከል የብዝሃ ኢኮኖሚ ዕይታው ውጤታማ መሆኑን ያመላክታል።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ጥቅል አገራዊ እድገት የግብርና መስክ 6 ነጥብ 1 በመቶ እድገቱን በመሸፈን ግንባር ቀደም ድርሻ ይዟል። ኢንዱስትሪ 4 ነጥብ 9 ከመቶ፤ የአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 6 በመቶ በመያዝ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በቱሪዝም መሰረተ ልማት ላይ የተሰሩ ስራዎች ሚና በጉልህ የሚጠቀስ ነው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በአጠቃላይ 16 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች። የተመዘገቡ ቅርሶች የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኚዎችን በመሳብ ለአገርና ለውጭ ምንዛሬ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
በተለምዶ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ የሚሰኘው የቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ በትኩረት ከተሰራበት በቀጥታና ተዘዋዋሪ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ለአገር እድገት ድርሻ ይኖረዋል። በ2015 ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው ጥቅል አገራዊ እድገት ውስጥ 7 ነጥብ 6 ከመቶ ድርሻን መያዙ ሁነኛ ማሳያ ነው።
በ10 ዓመት የልማት እቅዱ አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ቱሪዝም አንዱ ሆኖ መቀመጡም ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት በግልጽ ያሳያል።
የአገሪቱን የቱሪዝም አለኝታዎች በአግባቡ መለየትና ማልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሰረተ ልማት ማጠናከርና ተጨማሪ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን መገንባት፤ በአገሪቱ የሚገኙ አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን ማልማትና ነባር መዳረሻዎችን ማጎልበት በልማት እቅዱ በቱሪዝም ዘርፉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የቱሪዝም ምርቶችን ዓይነትና መጠን በማስፋፋት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ ውጤታማ የገበያ ትስስር፣ ብራንዲንግና ፕሮሞሽን ሥራዎችን በማከናወን አዳዲስ የቱሪዝም ገበያዎችን መፍጠርና የገበያ ድርሻን ማሳደግ፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ፣ በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለአገራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዛት በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት 1 ሺህ 348 በ2022 በጀት ዓመት ወደ 2 ሺህ 696 ለማሳደግ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ የጎብኚዎችን እርካታ መጠን ከ50 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ግቦች ተቀምጠዋል። በተጨማሪም 59 አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማትና በ40 ነባር መዳረሻዎች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስተዋወቅና የጉብኝት ባህል እንዲዳብር በማድረግ የጎብኚዎችን ቁጥር በ2012 በጀት ዓመት 23 ነጥብ 7 ሚሊዮን በ2022 በጀት ዓመት ወደ 70 ሚሊዮን ማሳደግ፣ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም የሰለጠነ የሰው ኃይልን ቁጥር በማሳደግ ሰልጥነው አገልግሎት የሚሰጡ ሙያተኞችን ከ23 ወደ 59 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተጥሏል።
በተጨማሪም ዘርፉን በማልማትና በማሳደግ ለዜጎች የሚፈጠረውን የስራ ዕድል በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት ከ1 ነጥብ 64 ሚሊዮን በ2022 በጀት ዓመት ወደ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለማሳደግ ታቅዷል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የጎብኚዎችን ቁጥር በዚሁ ጊዜ ከ850 ሺህ ወደ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በማሳደግ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ግብ ተጥሏል።
ይህንን ግብ ለማሳካት የሚያስችል የዘርፍ አደረጃጀትና አሰራር ማሻሻያዎች የሚደረጉ ሲሆን የመዳረሻ አስተዳደር ተቋም የመመስረትና የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከልን ወደ ኢንስቲትዩት የማሳደግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በእቅዱ ላይ ተቀምጧል።
በዚሁ ቅኝት መንግስት ለዘርፉ መነቃቃትና ለጎብኚዎች ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ተጨማሪ የመስህብ ስፍራዎችና የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በ2011 ዓ.ም የአገር ውስጥ ቱሪዝም ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መግባቱም የዚሁ አካል ነው።
ከ130 ዓመት በላይ ታሪክ ያላትን አዲስ አበባ የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማስፋት የሚያስችል ስራ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት አማካኝነት ሲከናወን ቆይቷል።
‹‹ገበታ ለሸገር›› በ29 ቢሊዮን ብር የአዲስ አበባን የወንዞች ዳርቻዎችና መናፈሻዎችን ለማልማት የተያዘ እቅድ እንደሆነ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በግንቦት 2011 ዓ.ም አዲስ አበባን ለከተማ ቱሪዝም በእጅጉ አመቺ ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ገቢ ለማስገኘት የ"ገበታ ለሸገር" መርሐ ግብርን ማዘጋጀታቸው የሚታወስ ነው።
ለመርሐ ግብሩ በተዘጋጀ የእራት ምሽት ከ200 በላይ ግለሰቦች፣ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶችና ተቋማት በዝግጅቱ ላይ መታደማቸው አይዘነጋም።
በመርሐ ግብሩ ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል በአዲስ አበባ የተገነቡት የእንጦጦ፣ የአንድነትና ወዳጅነት ፓርኮችም ይጠቀሳሉ።
ፕሮጀክቶቹ የቱሪዝም መዳረሻን ከማስፋት ባለፈ በርካታ የስራ እድል የፈጠሩ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ወሳኝ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት በ2013 ዓ.ም ወደ ገበታ ለአገር አድጎ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል። ጎርጎራ፣ ወንጪ-ደንዲና የኮይሻ ፕሮጀክቶች የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ስራዎች ሲሆኑ የብዝሃ ቱሪዝም ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
ጎርጎራ
ጎርጎራ ከጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ በ61 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኝ ውብ ከተማ ነች።
አጼ ሱስንዮስ ዋና ከተማቸውን በ1604 ከጉዛራ ወደ ጎርጎራ ከተማዋ ቀደምት የታሪክ ባለቤት መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ። ከተማዋ ታሪክ ጠገብ ስለመሆኗ በዙሪያዋ ያሉ ገዳማት፣ አድባራት፣ የነገስታት ቤተ-መንግስት ፍርስራሾች እና እደሜ ጠገብ እጽዋቶች ምስክር ናቸው።
በመዘንጋትም ይሁን በትኩረት ማጣት ጎርጎራ ዘመናትን የተሻገር የእርጅና ጫና ውስጥ ነበረች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያስጀመሩት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ግን ይህን ሁኔታ በመቀየር ለጎርጎራ ትንሳኤን ይዞ ብቅ ብሏል። ታሪኳን የሚያድስ ስሟን በደማቅ ቀለም የሚከትብ የቱሪዝም መሰረተ ልማት እየተገነባላት ይገኛል።
የከተማ ነዋሪዎችም የዘመናት ቁጭታቸው መልስ ያገኘበት ድንቅ ሁነት መምጣቱን በማሰብ "ጎርጎራ - የመጻዒ ዘመን ሙሽራ" ሲሉ ማሞካሸት ጀምረዋል።
የጎርጎራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬን እድልና የነገ ሕልም ደምሮ የያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአንድ ወቅት ፕሮጀክቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የገለጹ ሲሆን ጎርጎራ ውስጥ ታሪካችን፣ እድላችንና ሕልማችን አለ ብለዋል።
ይህ ታሪክ፣ እድልና ሕልም ዕውን ሊሆን ተቃርቧል፤ ምክንያቱም የጎርጎራ ፕሮጀክት የመጠናቀቂያው ጫፍ ላይ ደርሷል።
ወንጪ-ደንዲ
ወንጪ ሐይቅ ሌላው ደማቅ የኢትዮጵያ ገጸ-በረከት ነው። በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ ከአዲስ አባባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ተፈጥሮ እጅግ ያስዋበችው ስፍራ ነው፡፡
ወንጪ 3 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ ላይ ያለ ሐይቅና ፍል ውሃ ሲሆን በአካባቢውም ደን፣ ብርቅዬ አዕዋፋት እንዲሁም በሐይቁ ደሴት ላይ ታረካዊው የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ይገኛል።
በእሳተ ጎሞራ ከተፈጠሩ ሀይቆች መካከል አንዱ የሆነውና የሰከነው ወንጪ ሐይቅ በመንግስት የገበታ ለአገር እየለሙ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ነው፡፡
“የአፍሪካ ስዊዘርላንድ” በሚል ቅፅል ስሙ በጎብኚዎች ዘንድ የሚታወቀው ወንጪ ሐይቅ የተፈጥሮ ደን፣ ሞቃት ውሃ እና ፏፏቴ እንዲሁም ተወዳጅ የማር ምርት በውስጡ የያዘ ነው።
አካባቢው የተላበሰውን ማራኪ ገጽታ ተከትሎም እ.አ.አ. በ2021 በስፔኗ ማድሪድ ከተማ በተካሄደው 24ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ወንጪ ሐይቅ ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ አይዘነጋም።
ከመዲናዋ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ይሀ ውብ የቱሪዝም መንደር የሚገባውን ትኩረት ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።
አሁን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የፈጠረው ዕድል ወንጪ ደንዲ ሀይቅና አካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ውበት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚቀይር ሆኗል።
ኮይሻ
የኮይሻ ኢኮ-ቱሪዝም በኦሞ ወንዝ ላይ በተሰራ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የተሰራው ሰው ሰራሽ ሐይቅ ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሚገኝ ሲሆን ኮይሻ በሚል የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ግንባታ ስያሜ ሃላላ ኬላ ሪዞርት እና የመስህብ መዳረሻ ስፍራ ለምቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የዳውሮና ኮንታን አካባቢ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን የሚያገናኝ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የጊቤ-3 ኤሌክትሪክ ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የዳውሮ ንጉስ ካዎ ሀላላ የድንጋይ ካብ፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ከኮይሻ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን በፓርኩ ውስጥ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል።
የሃላላ ኬላ ሪዞርትም በአካባቢው የሚገኝ እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራን ለመጎብኘት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።
የኮይሻ ፕሮጀክት በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዳሉትም ኢትዮጵያ ልማቷን እያፋጠነች ሪቫን እየቆረጠች ወደፊት ወደ ብልጽግና መገስገሷን እንደምትቀጥል ማሳያ ነው።
ቀጣይ ገበታ ልትውልድ . . .
በገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚገታ አይደለም። በገበታ ለሸገር ተጀምሮ፣ በገበታ ለአገር አድጎ፣ በገበታ ለትውልድ ወደፊት ወደ ትውልድ የሚሻገር እንጂ።
መንግስት የተረሱ አልያም ከእይታ ውጪ ሆነው የቆዩ ውብ ስፍራዎችንና ቅርሶችን በማስተዋወቅ በማልማት በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ ታሪክ የማይረሳውን ሌላ አሻራ እያኖረ ነው።
"በገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክትም በአገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ስምንት የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ውሎ አድሯል።
ፕሮጀክቶቹም በትግራይ ክልል ገራ አልታ፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ በአማራ ክልል ሐይቅ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ፣ በአፋር ክልል የፓልም ፋርም እና በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚገነቡ ይሆናል።
የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም ለየአካበቢው ገጽታን በመቀየር ውብ የኢኮ-ቱሪዝም ምኅዳር በመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። የብዝሃ ኢኮኖሚ ዕይታው ትክክለኛና የተሳሰረ መሆኑንም በግልጽ ያረጋግጣሉ።
በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ስራዎች ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝነት አላቸው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እውን ለማደረግ የተጀመሩ ትልልቅ ስራዎችን ማገዝ ያሻል።