ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ያላቸው ህብረትና አንድነት ለሰላም ግንባታው መጠናከር ያለው ሚና እንዲጎላ አበክረው ሊሰሩ ይገባል

ሶዶ፤ ታህሳስ 10/2016 (ኢዜአ)፡- የኃይማኖት ተቋማት ያላቸውን ህብረትና አንድነት ለሰላም ግንባታው መጠናከር ያለውን ሚና  ለማጉላት አበክረው እንዲሰሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምስረታ ርዕሰ መስተዳድሩ እና  የኢትዮጵያ የሃይማኖት  ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። 

አቶ ጥላሁን መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት፤ የኃይማኖት ተቋማት ለዘመናት የቆየ እና የተጋመደ ህብረትና አንድነት አላቸው።

ይህም ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀው በተለይ  የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ተምሳሌታዊ ተግባር እንዲፈጽሙ አሳስበዋል። 

በመሆኑም የኃይማኖት ተቋማት አንድነትና መከባበርን ከማስተማር ጎን ለጎን ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን በንቃት ሊከላከሉ እንደሚገባም ተናግረዋል። 

በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ሂደት ላይ የኃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው በማስታወስ በቀጣይም ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአንድነት እንዲሰሩም አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤  ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን የሰላምና የመከባበር እሴት በማጠናከር  የሚገጥሙ ፈተናዎችን እንድትሻገር በማገዝ ገንቢ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሀይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት ከተወጡ ሀገራችን የሰላም እጦት ስጋት አይሆንባትም ያሉት ቀሲስ ታጋይ በዚህም ዘርና መሰል ሁኔታዎችን መነሻ የሚያደርጉ ልዩነቶችን ከማጥበብና ከማስወገድ አንጻር የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል። 

በመሆኑም ይህንን ሚናችንን ለሀገር ሰላምና ልማት መረጋገጥ በየተሰማራንበት አስተምህሮ ትውልድን በማነጽ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎችን የሀይማኖት ተቋማት በአስተምህሯቸው እንደሚደግፉ ተናግረዋል። 

በመድረኩም የምስረታ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትና የስራ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም