በኢትዮጵያ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀቶችን በማምረት የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላትና ለወረቀት ግዥ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን አዳል ኢንዱስትሪ ገለጸ፡፡
ኢንዱስትሪው ባቋቋመው ፋብሪካ ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በተደረገለት ሙያዊ ድጋፍ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት ማምረት መጀመሩን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የእንሰት ምርት ከምግብነቱ ባሻገር ተረፈ-ምርቱ ለመድኃኒት፣ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች ይውላል።
አሁን ደግሞ ለወረቀት ማምረቻ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግልም ነው የተገለጸው።
በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ዴሲሳ ያደታ እንደገለጹት፤ በእንሰት ተክል ላይ በተደረገ ጥናት ለወረቀት ማምረቻ በጥሬ እቃ ግብዓትነት እንደሚውል ተረጋግጧል።
የምርምሩን ውጤት መነሻ በማድረግም አዳል ኢንዱስትሪ የተሰኘ አምራች ኩባንያ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር በይፋ ወረቅት ማምረት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለወረቅት ግዢ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ የገለጹት ዶክተር ዴሲሳ፤ ወደ ምርት የገባው ኢንዱስትሪ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በተኪ ምርት ለማሟላት መስራት አለበት ነው ያሉት።
በአንድ ኢንዱስትሪ የተጀመረውን የማምረት ሂደት ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲሰማሩበት ይደረጋል ብለዋል።
የአዳል ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ አቶ አዳነ በርሄ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ለጋዜጣ፣ ለመጽሐፍ፣ ለካርቶንና ለመጠቅለያ የሚሆን ወረቀት ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።
ለወረቀት ምርቱ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለውን ተረፈ ምርት በዘላቂነት ለማግኘት በሀገሪቱ እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር በመፍጠር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የእንሰት ተረፈ ምርትን ለወረቀት ማምረቻነት መጠቀም የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚያቃልልም ገልጸዋል።
አዳል ኢንዱስትሪ በአማካይ በዓመት 30 ሺህ ቶን ወረቀት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በቀጣይ ይህን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር ምርቱን ወደ ውጪ አገራት የመላክ ዕቅድ ሰንቆ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡