አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት እንዲኖር የተሳታፊዎች ልየታ ስራ በክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተከናውኗል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት እንዲኖር የተሳታፊዎች ልየታ ስራ በክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተከናውኗል - ኮሚሽኑ
አዳማ ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት እንዲኖር የተሳታፊዎች ልየታ ስራ በክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መከናወኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለፀ ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያም ለኢዜአ እንደገለፁት የምክክር ሂደቱን አካታችና አሳታፊ ለማድረግ አሰራር ከመዘርጋት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በኮሚሽኑ ተከናውነዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ዕድሮች፣ የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተባባሪነት እንዲሳተፉና ኮሚሽኑን እንዲያግዙ በማድረግ ረገድ የተሻለ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።
በተከናወኑት ተግባራትም የሀገራዊ ምክክር ዓላማና ሂደቱን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ከሚደረገው ስራ ጎን ለጎን የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።
በእስከ አሁኑ ሂደት ተባባሪ አካላት በሀገራዊ ምክክር ዓላማና የተሳታፊዎች ልየታ ስነ ዘዴ ላይ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በድሬ ደዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በአፋርና ሶማሌ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር መላኩ፤ በደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ደግሞ የተባባሪ አካላት ስልጠና በመስጠት የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን ለ2ሺህ 500 የሚሆኑ ተባባሪ አካላት ስልጠና የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከክልሉ 8 ዞኖችና ከሸገር ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት በመጀመሪያው ዙር ስልጠና መሰጠቱን ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል።
በክልሉ የተባባሪ አካላት ስልጠና እንደተጠናቀቀ የተሳታፊዎች ልየታ የማከናወን ስራ በቀጣይነት ይከናወናል ብለዋል።
በዚህም በእስከ አሁኑ ሂደት በተሳታፊዎች ልየታ ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አቶ መላኩ አንስተዋል።
በአማራና ትግራይ ክልሎችም የተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ልየታ በቀጣይነት የሚከናወን መሆኑንም ኮሚሽነር መላኩ አመልክተዋል።