ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የቅመማ ቅመም ምርቶች ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርት ለማስጠበቅ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የቅመማ ቅመም ምርቶችን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መስፈርትን ለማስጠበቅ የሚያሰችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።  

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ድርጅቱ ወደ ውጪ የሚላኩ የቅመማ ቅመም ምርቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መስፈርት ሟሟላታቸውን ያረጋግጣል።

ለዚህም የተደራጁ እና ዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟሉ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች፣ የምግብ እና ግብርና ውጤቶች ፍተሻ ላቦራቶሪዎች እንዲሁም ግብዓቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ላኪዎች፣ አምራቾች እና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በምርቶች ደረጃ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተፈረመውን ስምምነት ለመተግበርም የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በአዲስ አበባ እና በክልሎች ባሉት 8 ቅርንጫፎች የጥራት ማረጋገጥ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የቅመማ ቅመም ምርቶች በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የጥራት ማረጋገጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ምርቶቹ የጥራት ማረጋጋጫ እንዲያገኙ መደረጉ አገሪቱ ከዘርፉ ምታገኘውን ገቢ እንዲጨምር ያስችላል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ናቸው።

ከዚህ በፊት የተወሰኑ ምርቶች ወደ ውጪ ከተላኩ በኋላ የጥራት ደረጃ መጓዳል ሲያጋጥም መቆየቱን ጠቅሰው ዛሬ የተፈረመው ስምምነት ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋል ብለዋል።

የቅመማ ቅመም ምርትን ከምርት እስከ ግብይት ጥራቱ እንዲጠበቅ የሚያግዝ ስለመሆኑ በማንሳት።

ኢትዮጵያ 16 የቅመማ ቅመም አይነቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ መሆኗንም ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም