ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት መፍታት የሚችሉት ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ ድርድር ብቻ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት መፍታት የሚችሉት ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ ድርድር ብቻ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት መፍታት የሚችሉት ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ ድርድር ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል ሲደረግ የነበረው አራተኛ ዙር ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመግለጫቸው፣ ድርድሩ ከቆመበት እንዲቀጥል የተደረገ ቢሆንም ያለስምምነት ተጠናቋል።
በግብጽ በኩል ድርድሩን የመቀጠል ፍላጎት ማጣት መስተዋሉን የገለጹት አምባሳደር ስለሺ፣ ኢትዮጵያ ማንኛውም ልዩነት ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ ድርድር መፈታት አለበት የሚል አቋም እንዳላት ገልጸዋል።
ግብጽ ከአራተኛው ዙር ድርድር በኋላ ዛቻ የሚመስል አቋም ማንጸባረቋን ጠቅሰው፣ በጋራ ከመልማትና በሰላም ከመኖር ውጭ የተሻለ አማራጭ የለም ብለዋል።