ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል በንግድ፣ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል-በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር

 

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል በንግድ፣ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ ።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት በኮሪያ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ሴኡል በተደረገው 2ተኛው የኮሪያ-አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ትብብር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች አንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት መንግስት እየወሰደ ስላለው ማበረታቻ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማትና የኢኮኖሚ እድገት የውጭ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነም አብራርተዋል።

በተለይ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ያላቸውን የጠነከረ ወዳጅነት በንግድ፣ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኮሪያ ሪፐብሊክ ለኢትዮጵያ እያደረገች የምትገኘውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች እንድታጠናክርም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነት በመጠቀም የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታታት እንደሚያስፈልግም ነው አምባሳደሩ ያከሉት።

የኮሪያ ሪፐብሊክ የንግድ ምክትል ሚኒስትር በያንግ ናይ ያንግ በበኩላቸው አፍሪካ በወጣት የሰው ሃይል፣ ባልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች አንዲሁም በበርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች የበለጸገች መሆኗን ተናግረዋል።

በጉባኤው የኮሪያ መንግስት ባለስልጣናትና ተወካዮች፣የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣የተቋማት ስራ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ የኮሪያ በለሀብቶች መሳተፋቸውን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም