ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ህዝባዊ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል

ነገሌ ቦረና ፤ ታህሳስ 9/2016 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከህዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስካሁን ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት  ገለጸ ፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገመቹ ገብረማሪያም እንደገለጹት በዞኑ ባሉ 10 ወረዳዎች ከህዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም እስካሁን በተደረገው ንቅናቄ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በስጦታና በቦንድ ሽያጭ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ ከዞኑ 26 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገመቹ ገብረማሪያም  ተናግረዋል ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የዞኑን ህዝብ ለድጋፍና ትብብር ማነሳሳቱን ጠቅሰው፤ ካለው መነሳሳትም ከዕቅዱ በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ፣ በዓይነትና በስጦታ እያደረገ ያለው ድጋፍ እስካሁን በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ተጠናክሮ እንደቀጠለ  ገልጸዋል፡፡

በድጋፉ ላይ ባለሀብቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና ሁሉም የህብረተሰብ ከፍሎች በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ በማከል፡፡

ባለፈው ዓመትም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድና በስጦታ መልክ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በድጋፉ ተሳታፊ ከሆኑት የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪና የዞን መንግስት ሰራተኛ አቶ ፍቃዱ ካሳ እንዳሉት ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት ሌላ በሀገር ገጽታ ግንባታ ልዩ ትርጉም ስላለው ለድጋፍና ትብብር መተባበር የዜግነት ግዴታ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

"በአሁኑ ዙር በራሴ ስም የ2 ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ፤ በቀጣይ ደግሞ በባለቤቴና በሶስት ልጆቼ ስም የመግዛት እቅድ አለኝ" ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን የ10 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ገመቹ ሀለኬ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በግል ተነሳሽነት የ6 ሺህ ብር፤ በአሁኑ ዙር ደግሞ የ1 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ገመቹ አክለውም ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን ከዚህም በላይ ተአምር የመስራት አቅም ያለን ህዝቦች እንደሆንን በተግባር ለዓለም አሳይተናል ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ህዝብን በማስተባባር ጭምር የሚያደርጉት ድጋፍ እንደማይቋረጥም ለራሳቸው ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም