በጅቡቲ ፓርላማ አፈጉባኤ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅቡቲ ፓርላማ አፈጉባኤ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው
አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 10/2016(ኢዜአ)፦ በጅቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሀመድ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው።
የልዑካን ቡድኑ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።
ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የጅቡቲ ፓርላማ ልዑክ ከአፈ ጉባኤ ዲሌታ በተጨማሪ የኢትዮ-ጅቡቲ የወዳጅነት ቡድን ሊቀ መንበር እና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የፓርላማ አባላትን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሀኑ ጸጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጅቡቲ ፓርላማ ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ከማጠናከር አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
እንዲሁም በአገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገርም ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
አገራቱ በቋንቋ፣ በባህል እንዲሁም በሃይማኖት የተቆራኙ እና ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአገራቱ ግንኙነት በጠንካራ እና በጽኑ መሰረት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም እንዲሁ።
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ እየተካሔዱ ያሉ የልማት ስራዎችን የሚጎበኝ ሲሆን የልምድ ልውውጥ መድረኮች እንደሚኖሩም ነው አምባሳደር ብርሀኑ የገለጹት።
ልዑካን ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሀመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
የጅቡቲ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲሌታ መሀመድ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።