ግብፅ ወደ ስምምነት እና ትብብር የሚደረገውን ጉዞ ተቃውማ መንገድ ዘግታለች - የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ ወደ ስምምነት እና ትብብር የሚደረገውን ጉዞ ተቃውማ መንገድ ዘግታለች - የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን አራተኛውን ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላለፉት 3 ቀናት በአዲስ አበባ ማካሄዳቸውን ገልጾ፤ እነዚህ አራት ዙር ድርድሮች የተካሄዱት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና በግብጹ ፕሬዚዳንት ዓብዱል ፋታህ ኤል ሲሲ የጋራ መግባባት መሆኑን አስታውሷል።
ሁለቱ መሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ ስራን አስመልክቶ የወጣውን ደንብና መመሪያ አጠናቅቆ ለማስቀጠል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እንዲደረግም ጥረዋል። ይህ ለአራት ዙር የዘለቀው ድርድር ሶስቱ ሀገራት በመካከላቸው ያሉ ዋና ዋና ልዩነት ፈጣሪ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እንዲያደርጉ ማገዙም እንደማይዘነጋ መግለጫው ጠቁሟል።
በእነዚህ አራት ዙሮች ኢትዮጵያ ከሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ዋና ዋና ልዩነቶችን ለመፍታት እና የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጋለች። በአንፃሩ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን ይዛ በመቀጠል ወደ ስምምነት እና ትብብር የሚደረገውን ጉዞ ተቃውማ መንገድ ዘግታለች ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አሞላል እና ዓመታዊ አሰራር መመሪያ እና ደንቦች ላይ የተደረገው ድርድር በሶስቱ ሀገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር እንጂ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያን መብት ለመንጠቅ ያለመ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ ላይ በመመሥረት የአሁንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል በግልፅ ማሳወቅ ትፈልጋለችም ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
እ.አ.አ 2015 ሶስቱ ሀገራት የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ለዚህ ድርድር መሰረት ነው ያለው መግለጫው ከዚህም በላይ ከ2020 ጀምሮ ጉዳዩን የያዘው የአፍሪካ ኅብረት ሦስቱ አገሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ መፍትሔ ሀሳብ እንዲመጡ ዕድል የሚፈጥርበትን መድረክ ማመቻቸቱን አስታውሷል።
ላለፉት 3 ቀናት የተካሄደው አራተኛው ዙር ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ ግብፅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ህብረት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን የሚጻረር መግለጫ አውጥታለች ያለው መግለጫው ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበባትን የተሳሳተ መረጃም አትቀበልውም ብሏል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እና በፍትሐዊ ድርድር የሶስቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ያላትን ቁርጠኝነት ይዛ እንደምትቀጥልም ሚንስቴር መስሪያቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።