ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

አዳማ ፤ታህሳስ 9/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ አካባቢ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከ40 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለዋግ ህዝብ ልማት ማህበር የቦርድ አባልና የጊዜያዊ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ በየነ አስረክበዋል።

ዋና ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ቢዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ ለዋግ ኽምራ አካባቢ በድርቅ ለተፈጠረው ማህበራዊ ችግሮች የአልባሳትና የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል።

የተደረገው ድጋፍ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ምስር፣ ቦለቄ፣ ፓስታ፣ የታሸገ ወተትና የምግብ ዘይትን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በዛሬው ዕለት 40 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ድጋፉ አቅም በፈቀደ መልኩ በቀጣይም የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የዛሬውን ጨምሮ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት አቶ ደበሌ፤ ይሄኛው ድጋፍ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል።

በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ዜጎች እንዳይጎዱ መተባበር አለብንያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ''ከተረፈን ሳይሆን  ለተቸገሩ ወገኖች ካለን ማካፈል አለብን'' ብለዋል።

የዋግ ህዝብ ልማት ማህበር የቦርድ አባልና የጊዜያዊ ድጋፍ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ በየነ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሳህላ፣ ዙቃላና ሌሎች የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ድርቁ ጉዳት አስከትሏል።

ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ አሁንም የተለያዩ ወገኖች እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም