ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ኃብቷን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን የማሳደግ ውጤታማ ሥራ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በፍትሃዊ የጥቅም ተጋሪነት የብዝኃ ሕይወት ኃብቶቿን እየጠበቀች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆነች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።  

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ጠቃሚ የዘር ባህሪ የያዘ የጄኔቲክ (ዘረመል) ቁስ ያላቸው ሲሆን፤ እነዚህ የዘረመል ኃብቶች ጥቅም ላይ መዋል ለአገር ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮ ያለው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ ይገለጻል።

የዘረመል ኃብት በዓለም ላይ እኩል በእኩል ተሠራጭቶ የማይገኝ በመሆኑ በተገቢው ጥቅም ላይ ካልዋለ ከምድር የመጥፋት አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።

የብዝኃ ሕይወት  ኃብት ወይም የማኅበረሰብ ዕውቀት መሰብሰብ፣  ማስተላለፍ፣ ወይም መጠቀም ለጥቅም ተጋሪነትና ለኃብት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ዓመታት ድርድር በኋላ የጄኔቲክ ኃብቶች ተደራሽነት እንዲሁም እኩልና ፍትሃዊ የኃብቶቹ ጥቅም ተጋሪነት ላይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የናጎያ ፕሮቶኮል(የሕግ ማዕቀፍ) ስምምነት ተፈርሟል።

የናጎያ ፕሮቶኮል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1992 ሕይወት ያላቸው ነገሮች ብዝኃነት ጥበቃ አስመልክቶ የተፈረመው ዓለም አቀፍ ስምምነት ደጋፊ ማዕቀፍ ነው።

ፕሮቶኮሉን ኢትዮጵያን ጨምሮ 92 አገራት የፈረሙት ሲሆን በተጨማሪም 50 አገራት ስምምነቱን በአገራቸው ፓርላማ አፅድቀዋል፤ የሕግ ማዕቀፉም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 አንስቶ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ኃብቶቿን በመጠበቅ ለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያዋለችው እንደምትገኝ ገልፀዋል።

ጤፍ፣ ግራዋ፣ ሬት፣ ቀረጥ፣ ሞሪንጋ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ዝንጅብል፣ አደይ አበባ፣ እርድ፣  የጥብስ ቅጠል(ሮዝመሪ)፣ ቁርቁራና ባክቴሪያዎች) በኢንስቲትዩቱ ፈቃድ ተሰጥቶ ጥቅም ላይ ከዋሉት በርካታ የብዝኃ ሕይወት ኃብቶች እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።

መናገሻ አካባቢ "ራይዞቢየም" የተሰኘ ባክቴሪያን በእንክብል መልክ ተዘጋጅቶ አፈር ውስጥ በመክተት ለአትክልቶች እድገት ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል።


 

ወጣቶች በጥቅም ተጋሪነት በማኅበር ተደራጅተው ፈቃድ በመውሰድ ባክቴሪያዎቹን እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ቢሾፍቱ አካባቢ አረንጓዴ ''አቂያ(ስፓይሮሊና) " የተሰኘ የአልጌ ዝርያ ለምግብነት እንደሚውልና ጥሩ ዘር ኢትዮጵያ ለተሰኘ ኩባንያ ፈቃድ መሰጠቱን ነው ዶክተር መለሰ ያብራሩት።

ቀረጥ(ኦስሪስ) የተሰኘ የእፅዋት ዝርያ  በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች በመሸጥ አርባምንጭ በኮስሞቲክስ ምርት ለተሰማራ ፋብሪካ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው ወደ ውጭ የሚልካቸው ምርቶች የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑና ወጣቶችም በማኅበር ተደራጅተው ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጭ ድርጅቶችም የብዝኃ ሕይወት ኃብቶችን እንዲጠቀሙ ፈቃድ በመስጠት ኢኮኖሚውን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ተቋሙ የብዝኃ ሕይወት ዝርያዎቹ በውስጣቸው ምን አለ?  ለምን አገልግሎትስ ይውላሉ?  የሚለውን እንደሚፈትሽ፣ እንደሚመረምርና እንደሚለይ አመልክተዋል።

ከቴክኖሎጂ አኳያም ተቋሙ ባሉት "የጂን" ወይም የዘረመል ባንኮች ዝርያዎችን የማራባትና የማብዛት ሥራን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጥቅም ተጋሪነት ያሏትን የጄኔቲክ ኃብቶች እንደ ራሳቸው አድርገው የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ተጠያቂ የማድረግ አሠራርን እንደምትከተል ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በብዝኃ ሕይወት ኃብቶቿ ያላት የጥቅም ተጋሪነት መልካም ጅማሮ እንደሆነና ወደፊት ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ አመላካች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም በናጎያ ፕሮቶኮል አማካኝነት የብዝኃ ሕይወት ፍትሃዊ ጥቅም ተጋሪነት ላይ እያከናወነች ያለችው ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም የኢንስቲትዩቱን የብዝኃ ሕይወት ኃብትን ወይም የማኅበረሰብ ዕውቀትን ለመሰብሰብ፣ ለመውሰድ፣ ለማስተላለፍ፣ ወይም ለመጠቀም የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል። 

የናጎያ ፕሮቶኮል አንቀጽ 15 ስለ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የጥቅም ተጋሪነት የሚያነሳ ሲሆን፤ ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅና መጠቀም እንዲቻል ከጄኔቲክ ኃብትና ከማኅበረሰብ እውቀት የሚገኘውን ጥቅም በሰጪና ተቀባይ አገራት መካከል ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል እንዳለበት ይደነግጋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም