ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ እሴቶችን በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል

አዲስ አበባ  ፤ ታህሳስ 9/2016 (ኢዜአ)፡- ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል ሲሉ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ምክር ቤት እና በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት "ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እና የባለድርሻ አካላት ሚና በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ሚና ከፍተኛ ነው። 


 

ባህላዊ የሽምግልና እና የእርቅ ሥርዓቶችን በማጎልበት አለመግባባቶችን በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች መፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚያግዝ አመላክተዋል።

ለዚህም  የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎችም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል። 

ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ከሳይንሳዊው የግጭት አፈታት ጋር በማቀናጀት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መሥራት ይገባል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ወሳኝና አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮችን በመለየት  በርካታ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 


 

ለአብነትም በሰላም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር መርህን መሠረት ያደረገ ግንኙነት በመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በሰላም ጉዳዮች ላይ የሚጠበቅበትን ሃገራዊ ኃላፊነት እና ሚና በአግባቡ በመወጣት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን  የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ ተናግረዋል።

የተለያዩ የባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ላይ በጋራ በመምከርና በኢትዮጵያ አውድ የተቃኙ ዘላቂ የሰላም መፍትሔዎችን  የመለየት ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአካባቢያዊ ግጭቶችን በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን መፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ያሉት በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ዶክተር ደሳለኝ አምሳሉ ናቸው።


 

በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች አለመግባባቶችን በማስታረቅ፣ መግባባትን በማሳደግ እና በማኅበረሰቦች መካከል ትብብርን በማጎልበት ረገድ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱን  የግጭት አፈታት ስልቶችን እውቅና መስጠት፣ ማጠናከር እና ማጎልበት እንደሚገባ በጽሑፋቸው አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም