በደቡብ ወሎ ዞን ከ26 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ከ26 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል
ደሴ ፤ታህሳስ 9 /2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከ26 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን የዞኑ ሥራና ሥልጠና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የዞኑ የሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በመድረኩ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ የዜጎችን የስራ አጥነትን ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከታቀደው ውስጥ ባለፉት አምስት ወራት ከ26 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ ለዚህም ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡
310 ሄክታር የመሥሪያና መሸጫ ሼድ መገንቢያ መሬት ማመቻቸት መቻሉን ተናግረዋል።
ወቅታዊና ሌሎችም ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም ችግሩን ተቋቁሞ ሥራ አጥነትን ለማቃለል የሚደረገው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አሊ መኮንን በበኩላቸው፤ ሰላምን ጠብቆ ዘላቂ ከማድረጉ በተጓዳኝ የዞኑ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የሥራ እድል ፈጠራውን ስኬታማ ለማድረግ እስከ ቀበሌ የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን ጠቅሰው፤ ለውጤታማነቱ የተጀመሩ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን ከአንድ ሺህ 800 በላይ ሰዎች የሥራ እድል ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የመቅደላ ወረዳ ሥራና ሥልጠና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ታደሰ ናቸው፡፡
ወቅታዊ ችግሮችን በመቋቋም የተሻለ ለመስራት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በህገ ወጥ የተያዙ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችን ከማስለቀቅ ባለፈ ተጨማሪ አዳዲስ ሼዶችንም ለመገንባት ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኩታበር ወረዳ ሥራና ሥልጠና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ ሽፈራው እንዳመለከቱት፤ በበጀት ዓመቱ በወረዳው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው 4 ሺህ 50 ዜጎች መካከል ከአንድ ሺህ ለሚበልጡት ማመቻቸት ተችሏል፡፡
ለዚህም ከአንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ ቀጣይም የተሻለ ለመስራት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዞንና የወረዳ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመልክቷል።