የክልሉን ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ልንሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ልንሰራ ይገባል
ጋምቤላ ፤ ታህሳስ 9 ቀን 2016(ኢዜአ) ፡- የክልሉን ባህላዊ የእርቅና የግጭት አፈታት እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ገለጹ።
በክልሉ ያለውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር የተዘጋጀ የባህልና የሰላም ፌስቲቫል ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ያለው ሰላም ይበልጥ በማጎልበት በድህነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ እውን ለማድረግ ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ መስራት አለበት።
በክልሉ ያሉትን ወርቃማ ባህላዊ የእርቅና የግጭት አፈታት እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ህዝቡ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትና የባህል ትስስርን ለማጠናከር የባህል ፌስቲቫሉ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ በበኩላቸው፤ የክልሉ ነባር ባህላዊ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ህብረተሰቡ የተገነቡ ነባር ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች የህዝቡን ደህነትና ሰላም አስጠብቀው የቆዩ ወርቃማ እሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ቢሮው እነዚህን ባህላዊ እሴቶች በማልማትና በመጠበቅ ለአብሮነትና ለሰላም ግንባታ የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የክልሉ ባህላና ቱሪዝም ቢሮ ዙአ / ZOA / ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የባህላዊና የሰላም ፌስቲቫል ላይ የማጃንግ ብሄረሰብ ባህላዊ እርቅ ስነ-ስርዓት የቀረበ ሲሆን፤ የክልሉ ነባር ብሄረሰቦች ባህላዊ ውዝዋዜዎች ቀርበዋል።