የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት እሰራለሁ-ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት እሰራለሁ-ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 9/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን እንዲፈጽም በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብስባ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ከመንግስት የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
ወይዘሮ ሜላተወርቅ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቦርዱን ለመምራት በህዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሰብሳቢዋ ቀደም ሲል የቦርዱን አፈጻጸም ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆኖ መጠናቀቁ ለዚያ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ በደቡብ ክልል የአደረጃጀት ህዝበ ውሳኔዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ የተቋማዊ ለውጡ ውጤት መሆኑንም ነው የገለጹት።
የቦርዱን ስኬቶች በማስጠበቅ ነጻ፣ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቀጥልና በህዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት ለመጨመር ከሌሎች አመራሮች ጋር በትጋት እንደሚሰሩም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ቦርዱ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ ቢሆንም የህዝብን ፍላጎት ከማርካት አኳያ የሚነሱ ክፍተቶችን መፍታትም ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆን አመልክተዋል።
በቦርዱ አሰራር ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል በተዘጋጁ የጥቆማ መስጫዎች ጥቆማ በመስጠት ወይም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚችል ጠቅሰው፤ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አዲሷ ተሿሚ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆናቸውን እንዲሁም ከትምህርት ዝግጅትና ከስራ ልምድ አኳያ ቦርዱን ለመምራት ብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሰብሳቢዋ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃትና በታማኝነት ሊወጡ እንደሚገባም ነው አባላቱ ያሳሰቡት።
ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣በፒስ ኤንድ ሴኩዩሪቲ ስተዲስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ማስተርስ ኦፍ ፐብሊክ አድሚንስትሬሽን ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት በባለሙያነትና በአመራርነት ያገለገሉት ወይዘሮ ሜላተወርቅ፤ ከየካቲት 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።