​​​​​​​በአካባቢያችን የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ስራ መቀየር የሚያስችል ሙያ እየቀሰምን ነው 

መቱ፤ታኅሣሥ 09/2016 (ኢዜአ)፦በአከባቢያቸው የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ስራ መቀየር የሚያስችላቸውን ሙያ እየቀሰሙ መሆናቸውን የመቱ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ሰልጣኞች ተናገሩ።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በ11 የስልጠና መስኮች ከ600 በላይ ሰልጣኞችን በንድፈ ሐሳብና በተግባር ተኮር ትምህርት በማሰልጠን ላይ መገኘቱም ተገልጿል። 

ከኮሌጁ ተማሪዎች መካከል አቤንኤዘር በፈቃዱ በኮሌጁ እየተከታተለ በሚገኘው የአውቶመካኒክ ትምህርትና ስልጠና ለነገ የሚጠቅመውን እውቀትና ክህሎት እያስጨበጠው መሆኑን ተናግሯል።

መምህራንም በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየሰጧቸው መሆኑን ገልፆ፤ ይህም ብቁ ባለሙያዎች ሆነው በመውጣት በአከባቢያቸው የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ስራ መቀየር የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጿል።

ከኤሌክትሪክሲቲ የትምህርት ክፍል ሰልጣኝ ለታ ነገሪ በበኩሉ በኮሌጁ በቂ የንድፈ ሐሳብና በተግባር የተደገፈ ትምህርት እያገኙ መሆኑን በማንሳት ይህም ወደፊት ላላቸው የስራ ፈጣሪነት ዕቅድ ውስጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው አንስቷል። 

በኮሌጁ እየተከታተሉ የሚገኙት ትምህርትና የሙያ ስልጠና ብቁና ስራ ፈጣሪ መሆን የሚያስችላቸው መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ የሰርቬይንግ ሙያ ሰልጣኝ ማርታ ሰለሞን ነች።

ሰልጣኞቹ እንዳሉት እየተከታተሉ ያሉት የሙያ ስልጠና በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በራሳቸው የሚተማመኑ ብቁና ስራ ፈጣሪ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ነው።

መምህር ልጃለም ታከለ ተማሪዎቹ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ቤቱ በሚያገኙት ሙያና ክህሎት ስራን ሳይጠብቁ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲችሉ መሆኑን ገልፀዋል።

በትምህርት ላይ እያሉም ሆነ በመስክ ምልከታ እና በተግባር ልምምዶች ጭምር ትምህርታቸውን እንዲያዳብሩ እየተደረገ መሆኑ ደግሞ ትልቅ ተስፋ እንደሆናቸው በማንሳት።

የመቱ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ተስፋዬ አባተ በኮሌጁ ከሚሰጠው የንድፈ ሐሳብ ትምህርት በላይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ላይ ትኩረት አድርገናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የስልጠና መስኮችን በተግባር በተደገፈ ልምምድ ለማስተማር ወደ ሌሎች ኮሌጆችና ተቋማት ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ ለሚሰጡ ስልጠናዎች በሙሉ በቂ የመለማመጃ ግብዓቶች ማሟላታቸውን ገልጸዋል።

በስልጠና መስኮቹ የሚሰጠው ትምህርት 30 በመቶው የንድፈ ሐሳብ ትምህርት ሲሆን ቀሪው 70 በመቶ ደግሞ በክፍል ውስጥ የተማሩትን በዎርክ ሾፖች፣ በአከባቢው በሚገኙ ፋብሪካዎችና ሌሎች ማበልፀጊያዎች በተግባር እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የተናገሩት።

በዚህም ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በተማሪዎቹ የስራ ውጤት የውስጥ ገቢውን የማሳደግ ስራዎችንም እየሰራ መሆኑን አክለዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት መቻሉን ገልጸው፤ በተያዘው የትምህርት ዘመን ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፈርኒቸር አንዲሁም በግብርና መስክ በሚሰሩ ስራዎች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ለማስገኘት ዕቅድ መያዙን ነው የተናገሩት።

በመቱ ከተማ የመቱ ፖሊ ቴክኒክ የትምህርትና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋምን ጨምሮ ስምንት የመንግስትና የግል የትምህርትና ሙያ ማሰልጠኛ ተቆማት የሚገኙ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ከ2ሺህ 600 በላይ ሰልጣኞች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም