የባቡር መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል- የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የባቡር መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል- የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር
ድሬደዋ ፤ ታህሳስ 9 /2016 (ኢዜአ)፡- ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግና ስኬት ሞተር የሆነውን የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ደህንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በባቡሩ መሠረተ ልማት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በድሬዳዋ ተወያይቷል።
ለውይይት በቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፤ በባቡር መሠረተ ልማት ላይ የስርቆት፣ ምሶሶ የመስበር፣ የትራፊክ አደጋ፣ በካሳ ጥያቄ ሽፋን ወንጀሎች የዘርፉ ተግዳሮት ሆነዋል።
ውይይቱን የመሩት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ እንደተናገሩት ፤ በብዙ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገንብቶ አገልገሎት እየሰጠ የሚገኘው ባቡር የኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ የልማት ሞተር ነው።
ይህንን የባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማስተጓጎል መንግስት ለአፍታ የሚታገሰው ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ባቡሩ የብሔራዊ ጥቅሞችም ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰው ፤ እየደረሰበት በሚገኘው ስርቆትና ችግሮች በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ እየተደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።
ችግሩን ለመፍታት ባቡሩ በሚያልፍባቸው የሲቲ ዞንና የምስራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖችና የድሬደዋ አስተዳደር አመራር አባላት በቁርጠኝነት በመስራት አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በድሬደዋ ስርቆትንና ጥፋትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የተከናወኑ ተግባራት መልካም መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ተሞክሮ በማስፋት የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ደህንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደንጌ ቦሩ ገለፃ፤ የየወረዳዎች አመራር አባላት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፤ በምንም አይነት ሰበብ ባቡሩ ለአንድ ደቂቃ መቆም የለበትም።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ፤ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረታዊ ሚና የሚጫወተውን የባቡር ደህንነት ለመጠበቅ ከተጎራባች ክልሎች የፀጥታና የፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የአመራር አባላት ቁርጠኝነት ለስራ መሳካት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የባብሩ መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ወሳኙ አካል በየደረጃው የምንገኝ አመራር አባላት የተጣለብንን ኃላፊነት በቁርጠኝነት አለመወጣት ክፍተት ነው ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት፤ የአመራር አባላት የባቡር መሰረተ ልማትን ለማስጠበቅ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራትን ለአፍታ መዘንጋት የሌለባቸው አገራዊ ኃላፊነት ነው።
የባቡሩ መስመር 220 ኪሎ ሜትር አቋርጦ እንደሚያልፍበት የተመለከተው የሲቲ ዞን የፍትህና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሣ ጠሃ በበኩላቸው ፤ የውጪና ገቢ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዘዋሪ በመሆን እያገለገለ የሚገኘውን የባቡር ትራንስፖርት በተሻለና በተቀናጀ መንገድ ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፌደራል ፖሊስ ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የየወረዳ አመራሮች በቀጣይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የተናበበና የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚተጉ ተናግረዋል።
የሲቲ ዞን የአገር ሽማግሌዎች የካሳ ክፍያ መዘግየትና የመጠን መለያየት እንዲስተካከል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ እንደ ችግር የቀረበውና ባቡሩ ለሚያደርሰው የትራፊክ አደጋ ተገቢውን ካሳ ሳይዘገይ የመስጠት ጥያቄዎች በተዘጋጀው የህግ ማዕቀፍ እንደሚፈታ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በውይይቱ ላይ ከዘርፉ ባለድርሻዎች ፣ ከድሬደዋ አስተዳደር ፣ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች እና ከሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን አስተዳደሮች የፍትህና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።