ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭትን ለመከላከል ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል-የጤና ባለሙያዎች 

ሮቤ፤ታህሳስ 9 /2016 (ኢዜአ)፡-እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት ለመከላከል ሕብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች መከሩ፡፡ 

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭትና የህክምና አገልግሎትን በማስመልከት የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

በሪፈራል ሆስፒታሉ የውስጥ ደዌ ህክምና እስፔሻሊት ዶክተር ወርቅነህ አለሙ እንዳሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት እየተስፋፋ መጥቷል። 

በተለይ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የልብና ካንሰርን የመሳሰሉ በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ 

ከዚህ በፊት በስፋት የሚታዩት ተላላፊ በሽታዎች እንደነበሩ ያወሱት እስፔሻሊስቱ አሁን ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በስፋት እየታዩ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

ዶክተር ወርቅነህ የዓለም ጤና ድርጅት ዳሰሳን በማጣቀስ እንዳሉት በዓለም በአሁኑ ጊዜ ከሚከሰቱት የሞት ምጣኔ መካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 71 ከመቶ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 43 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም፤ እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ለመከላከል ሕብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ 

የጎባ ራፈራል ሆስፒታል ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር አበሹ ጨመዳ በበኩላቸው፤ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን የመቆጣጠር ሥራ ስኬታማ ቢሆንም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ግን በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በመሆኑም፤ሕብረተሰቡ አመጋገቡን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማዝወተር እንዳለበት መክረዋል። 

ከዚህም ባለፈም በየጊዜው ምርመራ በማድረግ ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

በተጨማሪም፤ ስኳር፣ ጨው፣ ጮማና ቅባት ከበዛባቸው ምግቦች ራሱን በማራቅ ህብረተሰቡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እንዲጠበቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

ሆስፒታሉ በየዓመቱ ሁለቱ የባሌ ዞኖችን ጨምሮ ከሌሎች አጎራባች ዞኖች የሚመጡ ከ250 ሺህ ለሚበልጡ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ዶክተር አበሹ እንዳሉት በተለይ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሥርጭት ለመቀነስና የህክምና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ወደ ጤና ጣቢያዎች ወርደው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሽታዎቹ በሰዎች ላይ ከሚያስከትሉት ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጉዳታቸው ከባድ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም ናቸው። 

ዶክተር ጄይላን እንዳሉት፣ በሆስፒታላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም እየተደረገ ከሚገኘው ጥረት በተጨማሪ የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። 

በተለይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች በሰጡት ነጻ የምርመራ አገልግሎት ከ4ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አክለዋል። 

ከሮቤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መሐመድ ጣሂር በሰጡት አስተያየት፣ ''የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች በሰጡኝ ምርመራ የስኳር በሽታ እንዳለብኝ በመረዳት ህክምናዬን በአግባቡ እየተከታተልኩ ነው'' ብለዋል። 

''የጤና ባለሙያዎቹ በመከሩኝ መልኩ የአመጋገብ ሥርዓቴን በማስተካከሌ ጤንነቴ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል'' ሲሉም ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም