ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሻንጋይ ከተማ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2016(ኢዜአ)፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የልዑካን ቡድናቸው ከሻንጋይ ከተማ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም በአዲስ አበባ እና በሻንጋይ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት ከቀድሞ ይበልጥ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። 


 

ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፋይናንስ ፣ በንግድ ፣ በቴክኖሎጂ እና በማኑፋክቸርንግ ዘርፍ ባስመዘገበችው አስደናቂ ልማት ከምትታወቀው ከሻንጋይ ከተማ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሻንጋይ ከተማ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ማዕከል እንዲሁም ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ካለችው እና የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ጋር ተቀራርቦ መስራት የሁለቱን ከተሞች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።


 

በቀጣይም የእህትማማች ግንኙነት በመመስረት በንግድ ፣ በቱሪዝም ፣ በኢንቨስትመንት ፣ በቴክኖሎጂ ፣ በአቅም ግንባታ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የሁለቱም ከተሞች ከንቲባዎች ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም