አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ወጣቶች
አዲስ አበባ ፤ ታህሳሥ 9/2016 (ኢዜአ)፦አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሆኖ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ያለውን የኃሳብ ልዩነትና አለመግባባት በምክክር ለመፍታት በማለም ነው የተቋቋመው።
ይህንንም ተከትሎ አገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችሉ የተሳታፊዎች ልየታን ጨምሮ ምክክሩን ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል።
ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሰከነ መንገድ ከመወያየትና ከመነጋገር ውጭ የተሻለ አማራጭ አይኖርም።
ወጣቶቹ እንደሚሉት በተለያዩ ወቅቶች ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ሲያስተጓጉሉ ቆይተዋል።
ይህንንም ለማስተካከል ምክክሮችን በማድረግና ልዩነት በሚፈጥሩ ጉዳዮች ተወያይቶ እልባት በመስጠት በአገሪቱ ሰላምን ማስፈን ተገቢ መሆኑን ነው የገለጹት።
ከዚህም አንጻር አገራዊ ኮሚሽኑን መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ለዚህም በተለይም አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተግባራዊ ለሚያደርጋቸው ውይይቶች፤ ስኬታማ እንዲሆኑ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት ወጣቶች መካከል ወጣት አቤል ባደገ እንደገለጸው፤ አገራዊ ምክክር ለቀጣዩ ትውልድ ሰላሟ የተረጋገጠና በኢኮኖሚ የበለፀገች አገር ለማስረከብ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብሏል።
በመሆኑም ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እሆናለሁ ነው ያለው።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ውይይቶችና ምክክሮች ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም የሚለው ደግሞ ወጣት እንዳለ አለሙ ነው።
ምክክሩ በሃሳብ የበላይነት የሚመራና አገራዊ አንድነትን የሚያስቀጥል እንደሚሆን ያለውን ተስፋ ገልፆ፤ ምክክሩ ያነገበው ዓላማ ግብ እንዲመታ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጧል።
ወጣት ብሩክ ታደሰ በበኩሉ፤ እኛ ወጣቶች ትልቅ ዓላማ ላለው ለአገራዊ ምክሩ ስኬታማነት በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብሏል፤ እርሱም የድርሻውን እንደሚያበረክት ተናግሯል።
አገራዊ ምክክሩ በተለይም ወጣቱ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ልምድ የሚሰጠው መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት እንዳለ አለሙ ነው።
አገራዊ ምክክሩ በዋናነት ለወጣቱ በመመካከር ለችግሮች መፍትሔ የሚገኝበት መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህም እንዲሳካ እርሱን ጨምሮ ወጣቱ በቀዳሚነት መሰለፍ እንዳለበት ገልጿል።
ወጣት ብሩክ ታደሰ በበኩሉ፤ ወጣቱ ትውልድ በምክክሩ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ተናግሮ በአገራዊ ምክክሩ የሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ተሳትፎ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያለው።