ቀጥታ፡

ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ተሾሙ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 9/2016 (ኢዜአ) ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾሟል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ምክር ቤቱ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ከመንግስት የቀረበለትን ጥያቄ በአንድ ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከቦርዱ ሰብሳቢነት በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን ብርቱካን ሚደቀሳን የሚተካ ዕጩ ሰብሳቢ ለመለየት በቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 አንቀፅ 5 መሰረት ስምንት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ መልማይ ኮሚቴ መሰየማቸው ይታወቃል።

ኮሚቴው ባደረገው የጥቆማ መቀበል ሒደት ከደረሱት 56 ጥቆማዎች መካከል ለመጨረሻ ዙር አምስት ሰዎችን የመለየት ስራ አከናውኗል።

ከ5ቱ መካከልም ኮሚቴው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት ሁለቱን ለመጨረሻ ዙር ለይቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማቅረቡ ይታወቃል።

በዚህም ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ አበበ እና አቶ ታደሰ ለማ ገርቢ መስፈርቱን አሟልተው መለየታቸው በወቅቱ መገለጹ የሚታወስ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ስብሰባው የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው እንዲሾሙ የመንግስትን የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባላትም ዕጩ ሰብሳቢዋ ከትምህርት ዝግጅትና ከስራ ልምድ አኳያ ቦርዱን ለመምራት ብቁ በመሆናቸውና ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆናቸው ሊሾሙ እንደሚገባ በሀሳብ ደግፈዋል።

ምክር ቤቱም ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉን በአንድ ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ የቦርዱ ሰብሳቢ አድርጎ ሾሟል።

ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በፒስ ኤንድ ሴኩዩሪቲ ስተዲስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ማስተርስ ኦፍ ፐብሊክ አድሚንስትሬሽን ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን(በአሁኑ ጉምሩክ ኮሚሽን) ከጀማሪ የሕግ ባለሙያነት አንስቶ የኦፕሬሽን መምሪያና የሕግ መምሪያ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

በኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የትምህርት ስርዓትና የትምህርት መስኮችን መቅረጻቸው የተገለጸ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባል ሆነው አገልግለዋል።

የግል የሕግ ማማከር ተቋም በማቋቋም የስልጠናና የማማከር አገልግሎት፣ የሕግ ሰነዶች ዝግጅት፣ የድርድርና ግልግል አገልግሎት ለአገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የስትራቴጂና ፖሊሲ ሰነዶችን በመቅረጽ አገልግሎት መስጠታቸው ተመላክቷል።

ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ከየካቲት 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም