ቀጥታ፡

ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ 

አሶሳ፤ታህሳስ 9/2016 ዓ.ም(ኢዜአ)፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከከተማዋ ነዋሪዎቹ መካከል በሆቴል ሥራ የተሰማሩት ባለሀብት አቶ አብዱልማሙድ ኢብራሒም እንዳሉት የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ላለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን ለልማት አንድ ያደረገ ነው።

ለፕሮጀክቱ ቦንድ በመግዛትና ሌሎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ በገንዘብና በተለያየ መንገድ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሌላዋ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሊዲያ ታረቀኝ በበኩሏ "የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን አሻራችንን ያሳረፍነበት የጋራ ሃብታችን ነው" ብላለች።

"ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በተለይ እኛ ወጣቶች ዋነኛ ተጣቃሚዎች እንሆናለን" የምትለው ወጣቷ፣ ለግድቡ መጠናቀቅ ሁላችንም የምናደርገውን ድጋፍ ማጠናከር አለበን ብላለች። 

በግሌ የግድቡ ግንባታ ፍጻሜ እስኪያገኝ ድረስ ቦንድ በመግዛትና ገንዘብ በመለገስ እደግፋለሁ በማለትም ወጣቷ ቁርጠኝነቷን አረጋግጣለች።

በሕዳሴው ግድብ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጸዳለ አበራ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

"የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለፕሮጀክቱ መፋጠን የድርሻችንን እየተወጣን ነው" የሚሉት ነዋሪዋ፣  ለግድቡ ግንባታ ከደመወዛቸው ለአራት ጊዜ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

"እኛ ኢትዮጵያውያን በፈታኝ ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱን ገንብተን ለፍጻሜ ማድረሳችን የህብረታችን ውጤት ነው" ያሉት ወይዘሮ ጸዳለ፣ ለግደቡ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። 

"የሕዳሴው ግድብ ልማትን በማፋጠን ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዝ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ጎሹ ጅባት የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

አንድነታችንን በማጠናከርና እጅ ለእጅ በመያያዝ የግድቡን ግንባታ ከፍጻሜ እናደርሳለን ብለዋል፣

በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል።


 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግራኝ ጉደታ በበኩላቸው፣ በክልሉ በዚህ ዓመት 13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከህብረተሰቡ 700 ሺህ ብር መሰብሰቡን ጠቁመው፣ የተሽከርካሪ እጥረት ተገቢውን ቅስቀሳና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የንግዱን ማህበረሰብ፣ ባለሃብቱንና የመንግስት ሠራተኛውን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተብ ክፍል በማነቃነቅ ዕቅዱን ለማሳካት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሕሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በክልሉ እስካሁን ድረስ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም