ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳሥ 9/2016 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን አቢባቶው ዋኔ ጋር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከል፣ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋምና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመላክቷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚንስቴሩ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ወደ ስራ መግባቱንና አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትም ይህንኑ ስራ እንዲደግፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠይቀዋል።
የአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን አቢባቶው ዋኔ በበኩላቸው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰተን ለመከላከልና ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መንስኤዎችን መለየት የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ የፋይናንስ፣ የቁሳቁስ እና የቴክኒክ ሀብቶች ውስንነቶችን መቅርፍ በሚቻልበት ዙሪያም መክረዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ብሎ በለያቸው እና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።