ኢትዮጵያ በሁሉ አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች ለማሳደግ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁሉ አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች ለማሳደግ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 08/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በሁሉ አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮ ቻይና የወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ የተመራን ልዑክ ተቀብለው አነጋግረዋል።
በምክክራቸውም አምባሳደር ምሰጋኑ አርጋ የኢትዮጵያ እና ቻይና ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የትብብር ግንኘነት እንዳላቸው አውስተዋል።
ይህን ስልታዊ ግንኙነት ወደ ሁሉአቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ከፍ በማድረግ ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ነው የገለፁት።
ግንኙነቱን በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማጠናከር የግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወደ ቻይና በስፋት ለመላክ ማቀዷን ነው ያብራሩት።
በኢትዮ ቻይና የወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዡ ጁንጁን በበኩላቸው ኮሚቴው በኢትዮጵያ የሚገኘውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በማስተዋወቅ የቻይና ባለሀብቶች መጥተው እንዲሰማሩ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ ብለዋል።
አሁንም 22 አባላት ያሉት ልዑክ ይዘው መምጣታቸውን እና 10ሩ በኢትዮጵያ ገበያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።