ቀጥታ፡

በመዲናዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለማስወገድ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ውይይት አካሄደዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ሲሆኑ በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችና የሁሉም ክፍለ ከተሞች መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በእገታ ወንጀል፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ በተደራጀ ከባድ የዝርፊያ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ሞተር ሳይክል፣ ባጃጅ፣ የራይድ ታክሲዎችን ተጠቅመው የሰው ግድያ፣ የሞባይል ንጥቂያ እና ሌሎች ወንጀሎች ፈፅመዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ እና በርካታ የሺሻ ማስጨሻ፣ የጭፈራና የቁማር ቤቶች (betting) እንዲሁም ሕገ-ወጥ የንግድ ሱቆች ላይ በተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ እንዲዘጉ መደረጋቸውን ገልፀዋል።


 

እነዚህ ወንጀሎች ለኅብረተሰቡ የፀጥታ ሥጋት በማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተከታታይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ አንደሚቀጥል እና በየጊዜው ውጤቱ እየተገመገመ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

የራይድ ተክሲ፣ የሞተር ሳይክልና የባጃጅ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲይዝ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራና በወንጀል ተሳትፈው ከተገኙ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተነስቷል።

በከተማዋ በቀጣይ ለሚካሄደው ኦፕሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ መቅረቡን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም