ቀጥታ፡

ኢዜአ እያከናወናቸው ያሉ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)  እያከናወናቸው ያሉ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።


 

የመስክ ምልከታው አላማ ቋሚ ኮሚቴው በሚከታተላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት የታቀዱ ስትራቴጂክ እቅዶች እና የ2016 በጀት አመት እቅድ ግቦችና ተግባራትን አፈጻጸም በመመልከት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና የተቋሙ አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት የተቋሙን የሪፎርም ስራዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። 


 

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ኢዜአ  እያከናወናቸው ያሉ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በቋሚ ኮሚቴው የሚድያ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አቡኔ አለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢዜአ እያከናወናቸው ያሉ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። 

ተቋሙ ተጽእኖ ፈጣሪነቱን እና የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግ  ያከናወናቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ  ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስደናቂ መሆኑን ለመመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ተቋሙ እያዘጋጃቸው ያሉ የፓናል ውይይቶችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው  በቀጣይም  ተጠናክሮ  መቀጠል አለበት ብለዋል።

ተቋሙ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎችም  ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ከተቋሙ ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ የተጀመሩ ስራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የተኬደበትን ርቀት  አድንቀው አሁንም በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፉት 80 አመታት ትክክለኛና ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርግ የቆየ  አንጋፋ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም