የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን እያስፋፋሁ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን እያስፋፋሁ ነው - የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን
ሚዛን አማን ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፡- የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሰብል ዘር እርሻ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በሚዛን አማን ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አካሄዷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ውጤቶች ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች እያከናወነ ነው።
መሬት፣ ውሃና የሰው `ሃይልን አቅም አሟጦ ከመጠቀም ባሻገር፤ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂን ከሜካናይዜሽን ሥራ ጋር አቀናጅቶ መተግበር ለምርታማነት ዕድገት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም የግብርና ሥራዎችን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን በማስፋፋት ላይ ትኩረት መስጠቱን አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል።
ከተግባራቱ መካከል የምርጥ ዘርና መሰል የግብርና ግብዓቶችን አርሶ አደሩ በአቅራቢያው እንዲያገኝ የእርሻ ጣቢያዎችንና የምርጥ ዘር ማዕከላትን መክፈት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ኮካ በሚባል አካባቢ የሚጀምረው የሰብል ዘር እርሻ ልማት ለውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ የሚቀርቡ ሰብሎች ጭምር እንደሚመረቱበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
ለዚህ ሥራ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ከክልሉ መንግሥት መረከባቸውን ገልጸው፣ ፈጥኖ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችል ውይይት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አካሄደናል ብለዋል።
የኮካ እርሻ ጣቢያ ኮርፖሬሽኑ ምርትና አገልግሎቱን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት የያዘውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት ያደረገ መሆኑንም አቶ ክፍሌ አስረድተዋል።
እየታየ ያለውን የዘር አቅርቦት እጥረት ሚዛን ለማስጠበቅ በቅርብ ወደ ሥራ የሚገባው ጣቢያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በካፋ ዞን ውስጥ የተጀመረው የታማሻሎ የምርጥ ዘር ብዜት እርሻ ጣቢያ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን ለክልሉና ለአጎራባች ክልሎች እያቀረበ ሲሆን፣ ይህም ለክልሉ ሁለተኛ የሰብል ዘር እርሻ ጣቢያ መሆኑን ተናግረዋል።
እርሻ ጣቢያው በቀጣይ ለአካባቢው አርብቶ አደር የሚሆን መኖን ማልማት እንደሚጀምር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኑ ኮርፖሬሽኑ በአካባቢው እያመጣ ያለውን ልማት ውጤታማ ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የእርሻ ጣቢያው ለአካባቢው አርብቶ አደር የልማት ሥራን ከማላመድ ባለፈ፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድልን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን የሱሪ ወረዳ ነዋሪ አቶ ባርባኩ ኤለክዩብ ወደ አካባቢያቸው የሰብል ልማት የሚያካሄድ ተቋም በመግባቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ፈጥኖ ወደ ሥራ የሚገባ ከሆነ ተጨማሪ የልማት ተግባራትን የሚያከናውኑ ድርጅቶችን ወደ አካባቢው ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።