በመዲናዋ በህገወጥ ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 3 ሺህ 241 የቤቲንግ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በህገወጥ ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 3 ሺህ 241 የቤቲንግ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 08/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በህገወጥ ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 3 ሺህ 241 የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) ቤቶች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በሰጡት መግለጫ፤ እርምጃ የተወሰደባቸው ቤቶች ከተሰጣቸው የስራ ፍቃድ ውጭ ህገወጥ ተግባራት ሲፈጽሙና ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሰሩ የተገኙ ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ቤቶች ከተሰጣቸው ፍቃድ ውጪ ሺሻ ማስጨስ፣ ጫት ማስቃም፣ አልኮል መጠጥ ሲሸጥባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በተለይ ከትምህርት ቤቶች ከ200 ሜትር ራዲየስ በታች የሚገኙ፣ ከ21 ዓመት በታች ወጣቶችን የሚያጫውቱ እና በህጋዊነት ሽፋን ወንጀል ሲሰራባቸው የነበሩ በመሆኑ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
እርምጃው በህብረተሰቡ እና በከተማዋ ላይ የተፈጠረውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
በርካታ ወጣቶች ረጅም ጊዜ በስፖርታዊ የውርርድ ቤቶቹ በማሳለፍ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀንስ በማድረግና የወንጀል መፈጸሚያ ቦታዎች እስከመሆን መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
ተማሪዎች ትምህርታቸውን በማቋረጥ በዚህ ተግባር መሳተፋቸው፣ ብሄራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ከ21 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ውርርዱን እንዳይጫወቱ ካወጣው ደንብ በተጻራሪ ህጻናትን ጭምር ሲያጫወቱ ተደርሶባቸዋልም ነው ያሉት።
በክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ ህገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በተገኙት ላይ ቢሮው ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር፣ ከንግድ ቢሮ፣ ደንብ ማስከበር እና ከፖሊስ ጋር በመሆን እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።
በተለይ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ የስፖርታዊ ውርርድ ተቋማት በመማር ማስተማሩ ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ከህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ነበር ብለዋል።
እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ሃላፊዋ፤ ህብረተሰቡ ትብብሩን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።