ቀጥታ፡

የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል-ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፦  የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የስራ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮጵያና የሩሲያ ባለሃብቶች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ዕድሎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የኢትዮ -ሩሲያ ኢኮኖሚ ፣ሳይንስ፣ ቴክኒክና ንግድ ትብብር ኮሚሽን ሊቀመንበርና የሩሲያ የፌዴራል የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ኃላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ የተመራ የልዑካን ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ጊዜ ለልዑኩ የሩሲያ ባለሃብቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ሊሰሩ በሚችሉባቸው አማራጮች ላይ ሰፊ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ባለሃብቶቹ ኢትዮጵያ ኢንዱስትራይዜሽንን ለማስፋፋት እያደረገችው ያለውን ጥረት በሚደግፉ ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተነስቷል።

ከአራት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ልዑክ በሩሲያ ጉብኝት ማድረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በወቅቱ ለሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስላሉት የልማትና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ሰፊ ገለጻ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን አንስተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ በአካል በመገኘት በኢትዮጵያ ያሉትን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በተግባር እንደተመለከቱና ሀገሪቱ ምን አይነት ኢንቨስትመንት እንደምትፈልግ ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

ባለሃብቶቹ በማዕድንና ኢነርጂ የምርት ማሳደጊያ ኬሚካሎችና የግብርና መሳሪያዎች ምርት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውንም ነው ያብራሩት።

የሩሲያ ባለሃብቶች በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን ዕድል በመጠቀም መዋዕለ-ንዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ ነው አቶ መላኩ የገለጹት።

ጉብኝቱ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶች ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ መስራት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።


 

የሩሲያ የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ሃላፊ ኢቭጌኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች ብለዋል።

የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም በተለይም በሳይንስና ቴክኖሎጂ በግብርና እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድንና ኢነርጂ ሃብት ለዘላቂ ልማት ማዋል እንድትችልና የስነ ምድር አሰሳ የጥናት አቅሟን እንድታሳድግ አገራቸው የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር ሆና መመረጧ ከሩሲያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያስችላትም ነው የተገለጸው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም